ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን ጠ/ሚ ዶክተር አብይ ተናገሩ

(ኤፍ ቢ ሲ)- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

51ኛው የአፍሪካ የፋይናንስ የእቅድና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው በዋናነት የአፍሪካ ሃገራትን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ያሳድጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የጋራ ገበያ ምስረታ የሚረዳ እቅድን ማዘጋጀት አላማው ያደረገ ነው ተብሏል።

የጋራ ገበያው በፈረንጆቹ 2022 የሃገራቱን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ አሁን ካለበት 16 በመቶ ወደ 52 በመቶ ከፍ ለማድረግ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ ኢትዮጵያ በ44 የአፍሪካ ሃገራት የተደረሰው ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ስምምነቱ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ለአፍሪካ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል።

ከዚህ አንጻርም ሌሎች ሃገራት ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱን እንዲያጸድቁም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸው፥ የአፍሪካ ሀገራት ለአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት መተግበር ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ለአፍሪካውያን ካለው ጠቀሜታ አንጻር ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችልበት አግባብ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ዋና ጸሃፊዋ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚውን በማስፋት የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ምቹ የኢኮኖሚ ድባብ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ሀገራት በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ሰፊ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ጤናማ ኢኮኖሚን ለመገንባትም የግብር ገቢን ማሳደግ፣ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገበሩ ስራዎችን አፈጻጸም ማሻሻልና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውውርን መቆጣጠር ይገባልም ብለዋል።

በጉባኤው ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ለስራ እድል ፈጠራና ኢኮኖሚያውን ለማስፋት ባለው ጠቀሜታና አስተዋጽኦ ላይ ምክክር ተደርጓል።

በጉባኤው የትናንት ውሎ ዘላቂ ልማት፣ ግብርና፣ ትምህርትና የስራ እድል፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ጉዳይ እንዲሁም የሳህል ቀጠናና አካባቢው ላይ ትኩረት ያደረጉ ርዕሰ ጉዳዮች ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በተያዘው የፈረንጆቹ አመት 44 የአፍሪካ ሀገራት የአህጉሪቱን ነጻ የንግድ ቀጠና ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ኬንያ እና ጋና ስምምነቱን በማፅደቅ የመጀመሪያዎቹ ሃገራት ሆነዋል፤ ስምምነቱን ያጸደቁበትን ሰነድም ለአፍሪካ ህብረት ልከዋል።

ይህ ስምምነት ተግባራዊ ይሆን ዘንድም በጥቂቱ 22 ሃገራት ሊያጸድቁት ይገባል።

ጉባኤው በቀጣይ ነጻ የንግድ ቀጠናው አህጉሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት፣ ኢኮኖሚውን ለማስፋት እና በአጠቃላይ ለአህጉሪቱ ልማት ባለው ፋይዳ ላይ እንደሚመክር ነው የሚጠበቀው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.