ኤርሚያስ ለገሠ ፃፈ ወይስ ጣፈ?

ትላንት ያከበርነውን ዛሬ እያዋረድን፤ ነገ የምናዋርደውን ዛሬ እያከበርን መኖር

(አልአሚን ተስፋዬ) – የአቶ ኤርሚያስ ለገሰን መፅሐፍ አዲስ አበባ ውስጥ እንደልቡ ሲዘዋወር ስመለከተው መቼም አንድ ሚኒስቴር ዴኤታ ለመሆን ዳድቶ የነበረ ሰው የፃፈው መፅሐፍ ቁምነገር አያጣውም፤ ብዙ የማናውቀው ነገር ሊያሳውቀን ይችላል በሚል ነበር መፅሐፉን መግዛቴ፡፡

ገዝቼም አልቀረሁ “የመለስ ልቃቂት” በሚል የተፃፈውን ዳጐስ ያለ መፅሐፍ ከፊትና ከጀርባ እንዲሁም ማውጫው ላይ የተደረደሩትን ርዕሰ ጉዳዮች ስመለከት ያው ላለፉት ሃያ ዓመታት በግል ጋዜጠኞችና በመፅሔቶች ብቻ ሳይወሰን በመፃህፍት ጭምር አንድ ጊዜ “የሕወሓት የንግድ ኤምፓየር” በሚል ርዕስ የታተመ መጽሐፍ ሲቀጥልም እስክንድር ነጋ “ምርጫ 97” በሚል ባሳተመው መፅሐፍ ላይ እንደ አብይ ርዕስ የተነሳ፤ ከዚህም በላይ ሁሉም ተቃዋሚ የነበሩ እና የሆኑ ግለሰቦች የእጅ ማፍታቻ አድርገው ከሚያነሷቸው “ባንዲራ ጨርቅ ተባለ” … “አሰብ የኛ ናት” እና “መሬት ለሱዳን ተሰጠ” ከሚሉ የአማተር ፖለቲከኞች አሰልቺ እና ተደጋጋሚ ርዕሰ ጉዳዮች በማይተናነስ ሁኔታ የኤርሚያስም መፅሐፍ ሁሌም እንደ ዳዊት ለሀያ ዓመታት ሲደጋገም ስለኖረው እና ስለሚኖረው “የኤፈርት ጉዳይ” የተፃፈ መሆኑን ለመገንዘብ ደቂቃዎች አልፈጀብኝም፡፡

ቢሆንም ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ይቅርና በኤርሚያስ ደረጃ ፊደል ቀመስ የሆነ ሰው “ከሚበጀው የሚፈጀው” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው እና ሲፈልግ የደራሲው ሲያሻው የጋዜጠኛው ማስታወሻ እያለ የሚዘላብድ ደራሲ እንደጉድ በሚነበብበት ሀገር አሁን ቢያልፍበትም የኤርሚያስ መፅሐፍ ቢያንስ ከልብ ወለድነት የወጣ በመረጃ የተጠናቀረ በሕግ አግባብ የተደገፈ እና አነሰም በዛ በእውቀት የተሞላ ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡

ታዲያ እምነቴን ምን ዋጠው? መፅሐፉን ማንበብ እንደጀመርኩ ልክ ጭቃ እንዳይነካን ድንጋይ እየመረጥን እንደምንራመደው ሁሉ እውነተኛ ይሁኑ አይሁኑ እያቀረበ ያለውን መከራከሪያ ለማንበብ ስሞክር ንባቤን የሚያደነቃቅፉ በርካታ ተቀፅላዎች፤ እጅግ በጣም የወረዱ ስድቦች አገላለፆች እና አንድ በስነምግባር የታነፀ ሰው የሚፀየፋቸው በርካታ አሳቃቂ ሐረጎች የታጨቀ መፅሕፍ በመሆኑ ወደቀጣዮቹ ምዕራፎች እና ዋነኛ መከራከሪያዎች ለመዝለቅ ጭቃ ውስጥ እየተርመጠመጡ መቆየት እንደሆነ ግልፅ ሆኖ ታየኝ፡፡

በተለይም ከሁሉ ከሁሉ የከፋ የስብዕና ዝቅጠት ሆኖ ያገኘሁት ትላንት በወዳጅነትም ሆነ በስራ ባልደረባነት ማዕድ የተቋደሳቸውን፤ ሀሳብ የተጋራቸውን፤ ቤታቸው ገብቶ ሻሂ ቡና ያለባቸውን ሚስጥሩን እና ሚስጥራቸውን ያካፈሉትን ግለሰቦች መፅሐፍ ይዞ ከተነሳው የኤፈርት ጉዳይ በማይገናኝ ሁኔታ ስማቸውን ከነአባታቸው ጭምር እየጠቀሰ አንዱን በእውቀት ማነስ ሌላውን በሴሰኝነት ገሚሱን በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ በሚያሳው ባህሪ ከፊሎቹን ደግሞ በግል ህይወታቸው ውስጥ ሲያፈቅሩም ሆነ ሲፈቀሩ ሲዋደዱም ሆነ ሲጣሉ ያጋጠማቸውን ሚስጥራዊ ህይወት በአስከፊ ሁኔታ ገበናቸውን ሲዘከዝክ ለእንደኔ አይነቱ አንባቢ መረጃዎቹ ትክክል ይሁኑ አይሁኑ ሁለት ነገሮቹን በአፅንኦት እንዲያስብ ያደርጉታል፡፡

አንደኛ ኤርሚያስ በወዳጅነትም ሆነ በስራ ባልዳረባነት የቀረባቸውን ሰዎች በስራ ባሳዩት ጉድለት ሙስና እና ገደብ የሌለው ሐብት የማጋበስ አካሄድ ማጋለጡ በማስረጃ እስከአስደገፈው ድረስ ለሀገር የሚጠቅም እና እራሱም በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ በኩራት እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው በመሆኑ የምደግፈው ነው። ሆኖም ግን የእነዚህ ግለሰቦች የግል ሕይወት የግላቸው እና የብቻቸው መሆኑ እየታወቀ “እቤቱ ሄጄ ያጋጠመኝ እውነታ” አይነት አገላለፅ አንድም ትላንት ኤርሚያስ ያከብራቸው እና ይቀርባቸው የነበሩ ሰዎችን ዛሬ እንዲህ አድርጐ ማቅለሉ ዛሬ አጠገቡ ያሉ ወዳጆቹ እና የፖለቲካ ባልደረቦቹ ስለነገ ምን ዋስትና ይኖራቸዋል የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በተለይም የግል ሕይወታቸው ጉዳይ እጅግ በጥንቃቄ የተሞላ እንዲሆን ያስገድዳቸዋል። አንድ ምሁር በጥናታዊ ፅሑፋቸው ላይ እንደገለፁት ትላንት ያከበርነውን ዛሬ እያዋረድን ነገ የምናዋርደውን ዛሬ እያከበርን መኖር ባህላችን ካደረግነው ብዙ ከራርመናል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ማንኛውም የፖለቲካ ሰው ዋነኛ ትኩረቱ በሕዝብ ተጠቃሚነት እና በሀገር እድገት ላይ በመሆኑ ዋንኛው ማጠንጠኛው ህዝባዊነት፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና ፍትሐዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንደሚሆን ቢታመንም የግለሰቦችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠንካራም ሆነ ደካማ ጐን ሲያነሳ ዞሮ ዞሮ ለለውጥ ብቻ ሳይሆን ግለሰቦቹ ከለውጥ በኋላ ከስህተታቸው ታርመው የህግ ተጠያቂነት ካለባቸውም የህግ ቅጣታቸውን ጨርሰው በሰላም ከህብረተሰቡ ጋር እንዲኖሩ መፍቀድ ከአንድ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ አመለካከት ነው፡፡

ነገር ግን ልክ ተስፋዬ ገ/አብ እንደሚያደርገው ሁሉ የበርካታ ግለሰቦችን ስም እያነሱ መሀይም እና የመሳሰሉ መሳለቂያ አገላለፆችን ማብዛት አቶ ኤርምያስ የሚያስቡት ለውጥ ቢመጣ እንኳ ሰዎች ፊት በተለይም በዚህ መልክ ከተገለፁት ግለሰቦች ቤተሰቦቻቸው ወዳጆቻቸው እና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስነምግባር እና ጨዋነት ያላቸው ሰዎች ፊት እንደምን መቆም ይቻላል?

በሀገር ውስጥ አለ ያሉትን ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ማጋለጥ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ቢራቸውን እና በራቸውን ከፍተው የጋበዙዋቸውን የሥራ ባልደረቦቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን በዚህ መልኩ የግል ሕይወታቸው ውስጥ መግባታቸው መፅሐፉን በእጅጉ የጐዳው ሲሆን እራሳቸውንም /ያው በሂትደ በዕድሜ መግፋት መብሰላቸው ወይም መክሰላቸው አይቀርምና/ ለፀፀት እንደሚዳረጋቸው የታወቀ ቢሆንም ከሁሉ የከፋው ግን ዛሬ ከጐናቸው ያሉ ወዳጆችም ሆነ የስራ ባልደረቦች ነግ በኔ የሚል ዜማ ቢያንጐራጉሩ የሚፈረድባቸው አለመሆኑ ነው፡፡

እናም አቶ ኤርሚያስ ከእሳቸው በእድሜም ሆነ በልምድ ላቅ ያሉትን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ክፍሉ ታደሰ እና ሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች አመለካከታቸው ምንም ይሁን ምን በስነምግባር የታነፀ ሰው እስከመጨረሻው ድረስ ሳይጐረብጠው እና ሳይሳቀቅ መፅሐፋቸውን እንዲጨርሰው የማድረግ ጨዋነታቸውን አሳይተውናል፤ ሊመሰገኑም ይገባል፡፡ በመሆኑም አቶ ኤርሚያስ የፃፉትን መፅሐፍ አንብቦ ለመጨረስ በየምዕራፉ እና በየአንቀፁ የተሰገሰጉትን መርዛማ የስድብ መዓቶች አግባብነት የሌላቸው አገላለፆች እየተጨማለቁም ቢሆን ማለፍን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ አይነት መፃህፍት ከሚሰጡት ይልቅ የሚወስዱት ይበዛልና አቶ ኤርሚያስ ወደፊት ማንኛውንም ፁሑፉ ሲፅፉ ከመጣፍ ይልቅ መፃፍ ላይ ቢያተኩሩ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.