እለቱ በታሪክ ሲታወስ

(አዲስ ዘመን)-  በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ወራት መካከል አንዱ ይህ ያለንበት የግንቦት ወር ነው። ወሩ በዛሬው ዕለት ሲታወስም ለ17 ዓመታት የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት፤ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም ሃገር ጥለው የኮበለሉበት 27ኛ ዓመት ነው። ኮሎኔል መንግስቱ በመፈንቅለ መንግስት ንጉሰ ነገሥቱን ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴን በመገልበጥ የወታደራዊው የደርግ መንግስት ፕሬዚዳንት በመሆን ነበር በ1967ዓ.ም ስልጣን የጨበጡት። ኢትዮጵያን እስከ 1983ዓ.ም ሲያስተዳድሩ ከቆዩ በኋላም ግንቦት 13 ቀን አገር ጥለው መኮብለላቸው ተሰማ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታም በሌትናንት ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ «አብዮቱና ትዝታዬ» በሚል በ2008ዓ.ም ከታተመው መጽሃፍ ለንባብ እንዲመች አጥሮ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ማክሰኞ ግንቦት 13 የፕሬዚዳንቱ ልዩ ረዳት ሻምበል መንግስቱ ገመቹ ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ ደርሶ ከዚያም ወደ አስመራ ደርሶ መልስ የሚበቃ ነዳጅ የሞላ አንድ ዳሽ 5 አውሮፕላን እንዲዘጋጅ ያዛል። ወደ ሁለት ሰዓት ገደማ ፕሬዚዳንቱ ከተመረጡ አጃቢዎች እንደዚሁም ከሶስተኛ ክፍለ ጦር የመጣና የቅርብ አጃቢያቸው ከነበረው ከሻምበል ደመቀ ባንጃው ጋር በመሆን በኮሎኔል ተስፋዬ መሪነት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመድረስ ተዘጋጅታ ትጠብቅ ከነበረችው አውሮፕላን ተሳፈሩ።
ፕሬዚዳንቱን የያዘችው ዳሽ 5 አውሮፕላን ብላቴን ለማረፍ ስትቃረብ ፕሬዚዳንቱ የአውሮፕላን አብራሪውን ኮሎኔል መኮንን አዳሳን ጠርተው ኬኒያ ናይሮቢ ዛሬውኑ በአስቸኳይ ስብሰባ አለኝ በማለት በቀጥታ ወደ ናይሮቢ እንዲያመራ ትዕዛዝ ሰጡት። ኮሎኔሉም ለዚህ በረራ ያልተዘጋጀ መሆኑንና የበረራ ካርታ አለመያዙን ቢገልጽም በሚችለው ሁሉ እንደምንም ብሎ እንዲሞክር፤ በጣም ምስጢር ስለሆነም የሬዲዮ ግንኙነት እንዳያደርግ አዘዙት። እንደአጋጣሚ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመብረር ላይ ስለነበር ሬዲዮ ግንኙነት በማድረግ የበረራ መስመሩን አስተካክሎ ከቀኑ 6ሰዓት ከ15 ኬኒያታ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ቻለ።
የኬኒያታ አየር ማረፊያ ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኗ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን መያዟን እንጂ የባለስልጣኑን ማንነት ስላላወቁ አውሮፕላንዋ ካረፈች በኋላ ፕሬዚዳንቱ ሳይወጡ ለረጅም ጊዜ ቆዩ። ከዚያም በአየር መንገዱ ባለስልጣናት በኩል በተደረገው ግንኙነት ለፕሬዚዳንት አራፕ ሞይ ከተነገራቸው በኋላ ወደ ኬንያ ቤተመንግስት አመሩ። እዚያው ቤተመንግስት እያሉ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ የነበረው ዶክተር መስፍን ረታ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መውረዳቸውን የሚገልጽ ቴሌግራም በውጪ ጉዳይ በኩል ይደርሰዋል። ይህንኑም ይዞ በመሄድ ለፕሬዚዳንቱ በንባብ አሰማቸው። እሳቸው ግን ይህ ሲነገራቸው ገንዘብ የያዙበትን የእጅ ቦርሳቸውን (ብሪፍ ኬዝ) በማሳየት መሳሪያ ለመግዛት ወደ ኮሪያ በማምራት ላይ መሆናቸውን እና የዚህ ዓይነት ቴሌግራም መተላለፉ ያሳዘናቸው መሆኑን ገለጹለት። ከዚህች ደቂቃ በኋላ ኮሎኔል መንግስቱ የኢሠፓ ዋና ጸሃፊ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና የኢሕዲሪ ፕሬዚዳንት ሳይሆኑ ስደተኛው መንግስቱ ሆኑ። ማምሻውንም ፕሬዚዳንት አራፕ ሞይ ባዘጋጁላቸው አውሮፕላን ወደ ስደት መኖሪያቸው ዝምቧቡዌ አመሩ።
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመንግስት ምክር ቤት የሚሰጥ መግለጫ እንዳለ እየደጋገመ ሲገልጽ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ «ጦርነቱ ያስከተለው ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቀርና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሃገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌትናንት ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ተክተው ይሰራሉ» የሚል አጭር መግለጫ አስተላለፈ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.