ከሱዳን የሚገባው ቀይ ሽንኩርት በመስኖ አልምቶ ለመተካት እየተሰራ ነው ተባለ

(ኢዜአ)- ከሱዳን በመተማ በኩል ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የቀይ ሽንኩርት ምርት በመስኖ አልምቶ ለመተካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ልኡል አበራ እንደተናገሩት በዞኑ መተማ፣ ቋራ፣ ጠገዴና ምእራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ለቀይ ሽንኩርት ልማት ተስማሚ ናቸው፡፡

በእነዚህ ወረዳዎች የሚገኙ ወንዞችን በመጠቀም ዘንድሮ በ5ሺ 387 ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርትን በመስኖ የማልማት ስራ ተጀምሯል፡፡

በመስኖ ከሚለማው ማሳም 600ሺ ኩንታል የቀይ ሽንኩር ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህም ከሱዳን በመተማ በኩል በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመተካት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በክረምት ወራት የሚፈጠረውን የቀይ ሽንኩርት እጥረት ለማቃለልም በመኸርም ጭምር በማምረት ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት የታቀደ ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 20 ሺህ ሄክታር የሚሆን ኩታል የገጠር መሬት በነጭ ሽንኩርትና በቲማቲም ይለማል፡፡

ከ350ሺ በላይ አርሰአደሮች ከሚሳተፉበት ከዚህ የመስኖ ልማት 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የመተማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ ባለሙያ አቶ ጌትነት ካሳሁን በመተማ በኩል የሚገባውን የቀይ ሸንኩርት በአካባቢ ሽንኩርት ለመተካት በ350 ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርት በመስኖ እየለማ ነው፡፡

”ወረዳው ከሱዳን ጋር ሰፊ የድርበር ግንኙነት ያለውና ተመሳሳይ የስነ ምህዳር ባለቤት ነው” ያሉት ባለሙያው በወረዳው እስከ 6ሺ ሄክታር የሚገመት ለሽንኩርት ልማት ተስማሚ መሬት እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በመተማ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ከፍያለው ቢተውና ሰመረ ሞገስ በሰጡት አስተያየት ወረዳውን አቋርጦ የሚፈሰውን  የጓንግ ወንዝ ለመስኖ በማዋል ሽንኩርት ለማልማት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.