ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ የአፍሪካ አዳራሽ በአዲስ መልክ እድሳት ሊደረግለት ነው

(ኢዜአ)- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ እድሳት ሊደረግለት መሆኑ ተገለጸ።

አዳራሹ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ የአፍሪካን ባህል፣ ታሪክና የኪነ ህንጻ ጥበብን ባማከለ መልኩ የተገነባ ነው።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ እድሳቱ ያስፈለገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያሉትን ተቋማት ለማዘመን በያዘው እንቅስቃሴ መሰረት ነው።

እድሳቱንም ኮሚሽኑ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከዓለም አቀፉ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ዩኔስኮ ጋር በመተባበር እንደሚያስፈፅመው ነው የተገለጸው።

የእድሳት ፕሮጀክቱ ስምምነትም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል እንደሚደረግም በመግለጫው ተብራርቷል።

ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ መስፈርትን ባሟላ መልኩ እድሳቱ የሚከናወን ሲሆን፤ እድሳቱ በአዳራሹ የሚገኙና የአፍሪካን ባህላዊና ታሪካዊ ሁነቶችን የሚያሳዩ ንድፎች ይዞታቸውን እንዳይቀይሩ በጥንቃቄ እንደሚከናወን በመግለጫው ተመላከቷል።

የአዳራሹ መታደስም እነዚህን ታሪካዊ ንድፎች ይበልጥ ለቱሪስት መስህብ ግልጽ እንደሚያደርጋቸውም መግለጫው አትቷል።

በተጨማሪም ቋሚ የኤግዚቢሽን ማዕከል እንዲኖረው መደረጉ የቱሪስት መዳረሻነቱን ይጨምርለታል ነው የተባለው።

አዳራሹ  በቅጥር ግቢው ከሚገኙ ሃያ ህንፃዎች አንዱ ሲሆን ከንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በተለገሰ ቦታ ላይ እ.ኤ.አ. በ1960 የተሰራ ነው።

በአገልግሎቱ ዘመንም ትልቅ አበርክቶ የነበረው ይህ ህንፃ  እ.ኤ.አ. በ1963 ለተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የትውልድ ቦታም ነበር።

Leave A Reply

Your email address will not be published.