ካነበብኩት: “ኢትዮጵያዊነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?”

(ሸጊት ከድሬ) – የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ከዚህ በፊት የተመለከትናቸውን በሥልጣን ኤሊቶች መካከል በተለያዩ ጊዜያት ከተደረጉ ጊዜያዊ መሸነጋገሎች ያለፈ በመጨረሻ በተቻለ መጠን በአዲስ ሕገ መንግሥት ተግባቢነት ፎርሙላ በሚቋጭ እስትራቲጂካዊና ታሪካዊ ሽርክና መፈጣጠም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ በተቻለ መጠን የብዙዎቹ ስምምነት የታከለበት የተቋጠረና የተገመደ መሆን ይኖርበታል፡፡ በተቻለ መጠን የብዙዎቹ ያልኩት አለምክንያት አይደለም፡፡ በሁሉም ዓበይት የሕዝባችን ጉዳዮች ስምምነተ ኩሉ (ኮንሰንሰስ) ላይ ሊደረስ እንደማይቻል እሙን ስለሆነ ነው፡፡ አብዝሃነታችንን እናስተናግዳለን ብሎም እናስተዳድራለን ካልን ልዩነቶች መኖራቸውን መቀበል ነው ቀዳሚው ስምምነት መሆን ያለበት፡፡

ኢትዮጵያዊነት እንደ አንድ አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት እንዲያስተሳስረን ከተፈለገ ትክክለኛ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ቅርስ ውርሳዊና እሴታዊ ይዘቱ በውልና በቅጡ መታወቅ ሊኖርበት ነው፡፡ በአገር ልጅነት ተጋርዮች ላይ የተመሠረተ አሰባሳቢ ማንነት ስንል ስለ የትኛው አገር እንደምንነጋገር በማንም ዘንድ ብዥታ ሊኖር አይገባም፤ አይቻልምም፡፡ የምንነጋገረው ኢትዮጵያ ስለምትባለው አገር ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስለሚል ሕዝብ እጣ ፈንታ ነውና፡፡ ጉዳዩ ኢትዮጵያ ስለምትባለው አገር ከሆነ ዘንዳ ኢትዮጵያዊነት ከኢትዮጵያ ወገንተኛነት ተለይቶ ሊታይ ይችላል ወይ? የሚል ጥይቄ ሊከተል ነው፡፡ ተገቢም ነው፡፡ መልሱ ኢትዮጵያ አገር ናት፤ ኢትዮጵያዊነት ግን ግለሰብ በምርጫውና በገዛ ፈቃዱ የሚላበሰው ወገንተኛነት ነው፡፡ ልክ የኦሮሞ ብሔርተኛነት፣ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነትን እንደ አንድ ተፈታታኝ ተግዳሮት አድርጎ እንደሚፎካከረው ሌሎች ብሔርተኛ ስሜቶችና ርዕዮተ ዓለሞችም ኢትዮጵያዊነትን ይጋሩታል (ተግዳሮት ይደቅኑበታል)፡፡ ለምሳሌ ኦሮሙማ የተሰኘው የኦሮሞ ብሔርተኛ አይድዮሎጂ ኢትዮጵያዊነትን የሚፃረር አመለካከት ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ተልእኮ ይዞ የተጠነሰሰ የፖለቲካ እንቅስቃሴም ጭምር ነው፡፡ አይድዮሎጂ ደግሞ ሁሉን ገዢ መሠረታዊ አመለካከት ስለሆነ ግለሰብ በወገንተኛነት ይቀዳጀዋል እንጂ አይወለዱበትም፡፡ ማን፣ ማንን ቢወልድ ዓይነቱ የዘር ሐረግ ቆጠራ አያቆራኘውም፡፡ ግለሰቡም ሆነ ስብስቡ ለአመለካከቱ ይወግኑለታል እንጂ አብረውት አይወለዱትም፡፡ ምክንያቱም ብሔርተኛነት በመሠረቱ አመለካከትም እሴትም ነውና፡፡ የኢትዮጵያዊነትን ትክክለኛ ይዘት መፈተሽ፣ መመርመርና ማወቅ ሊሞከር ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ “ኢትዮጵያዊነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?” ተብሎ ቃለ መጠይቅ ብጤ ተደርጎ ውጤቱም የሳይንሳዊ አጠናን ዘዴን ተከትሎ ቢጠናቀር፣ የኢትዮጵያዊነትን ትክክለኛ ይዘት የማግኘቱን ጉዞ ፈር እናስይዛለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብዙ አገሮች የዚህ ዓይነቱ የግለሰብ ወገንተኛነት ምርጫ ማወቂያ መጠይቅ ማጠናቀር የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ምንም ነውርነት የለበትም፡፡

ፈረንጆቹ አኔክዶታል(Anecdotal) የሚሉትን አስረጅ አግባብ ነው በዚህ መጽሐፍ ብዙ ጊዜ የተጠቀምኩት፡፡ ስልቱ አንዱን ጭብጥ በእርግጠኛነት እውነት ነው ብሎ ለአንባቢያን ለማሳመን ብቃት ያለው ሳይንሳዊ ምርምርና አመክኒዮአዊ አካሄድ አለመሆኑን ግን አልዘነጋሁም፡፡ አንድን ነጥብ ለማብራራት እንጂ የአንድን ጭብጥ ትክክለኛነት በማያወላዳ መልኩ ያረጋግጣል በሚል እርግጠኛነት አይደለም አስረጅም ምሳሌዎችን የማቀርበው፡፡ ለምሳሌ፣በአንድ ወቅት “ከረንት ኦፌሪስ” በተሰኘው በታዋቂው የኢትዮጵያውያን ፓልቶክ ሩም ውስጥ በታዋቂዋ አድሚን “ኢትዮጵያዊነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?” የሚለው ጥያቄ ተወርውሮ ከታዳሚዎች የተሰጡ መልሶችን እያዳመጥኩ ነበር፡፡ መልሶቹ በጣም በሚያስገርም መልክ ጉራማይሌና ዥንጉርጉር ነበሩ፡፡ በእኔ እይታ ቃሉ ራሱ እንደማንኛውም በ “ዊነት” የሚያልቁ ፅንሰ ሐሳቦች ሁሉ የአመለካከት ተሸካሚ እንጂ የገቢር ምልክትነት እንዳለው የሚፈነጥቅ መልስ አላገኘሁበትም፡፡ ሲጠቃለል ለብዙ መልስ ሰጪዎች ኢትዮጵያዊነት የምንታወቅባቸውንና የምንኮራባቸውን አብሮ መብላትና መጠጣትን የመሳሰሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን ያካትታል፣ ስሜት ዘለል ርዕዮተ ዓላማዊ አድማሱን እንዲያካትት የተደረገ ሙከራ እምብዛም ነበር፡፡

ከሁሉ በላይ ያስደመመኝ ግን አንድ መልስ ሰጪ “ኢትዮጵያዊነት !?…ኢትዮጵያዊነት !?…ኢትዮጵያዊነት !?… እንዲያው እንዲያው ዝም ነው!” ብሎ ዝም ያለው ተናጋሪ መልስ ነው፡፡ በወሲብ ተራክቦ ወቅት ሰውነት ከሚወር ንዝረታዊ ስሜት ጋር ያመሳሰለው መላሽም ነበር፡፡ ይህን በመሰሉ ትርጉሞቹ ኢትዮጵያዊነት ተፎካካሪ ፀረ ኢትዮጵያዊ አይድሎጂዎችን መክቶ (በአስተሳሰብ ደረጃ) የሚመለስ የአሰባሳቢ ማንነት አቃፊ ደጋፊ ርዕዮት ሊሆን ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ይጭርብኛል፡፡ በአይድዮሎጂ ውስጥ ስሜቶች መካተታቸው ባይካድም ስሜት ብቻ የአገር ልጅነት ተጋርዮሽ አሰባሳቢ ማዕቀፍን ተክቶ ሊያገለግል መቻሉን እጠራጠራለሁ፡፡ የግድ የአሰባሳቢ አናሳሮቹ ይዘት በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እኔ ራሴ ከበርካታ ወዳጆቼ ጋር በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ያደረግኩት የሐሳብ ልውውጥ ትክክለኛው ርዕዮተ ዓለማዊ ይዘቱ የግድ መታወቅ አለበት ብቻ ሳይሆን መጎልበት ይኖርበታል የሚለውን አመለካከት አጠናክሮልኛል፡፡ በሌላ በኩል፣ እንደ አንድ አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት እንዲያገለግል ከተፈለገ፣ የተለያዩ ዝልዝል ማንነቶች ተግዳሮቶች ሆነው ሲፈታተኑ እነሱንም ጭምር አቅፎ ደግፎና አካቶ መራመድ አለበት እንጂ እነሱን የሚደፈጥጥ ወይም የሚክድ መሆን የለበትም፡፡ ያን አማራጭ ከተከተሉ ፋይዳው አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ኢትየጵያዊነት ለሁሉም ማንነቶች አቃፊ ደጋፊ ሆኖ መቅረብ መቻል አለበት፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞችም ሆኑ የሌሎች ብሔረሰቦች ሥልጣን ኤሊቶች ኢትዮጵያዊነት የአማራ ብሔረሰብ የካልቸር ኤሊቶች የቀድሞ የበላይነታቸውን ለማስቀጠል የመሸጉበት ካልቸራዊ ቅርስ ውርሳዊ ገዢ መሬት እንደሆነ ካዩትና ከወዲሁ ካጣጣሉት ራሱን የቻለ አስቸጋሪ ተግዳሮት ይጋረጥበታል፣ ያለ ጥርጥር፡፡ በተግባር የምንመለከተው ከዚህ እምብዛም የተለየ ሁኔታ አይደለም፡፡ በማህበራዊ ሳይንስ በተለይም በማንነት ፖለቲካ ውዝግብ መስክ መምሰል (ፔርሰፕሽን )ከተዳሳሽ ገሃድ እውነታ እኩል ሚዛን የሚያነሳበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ደግመን፣ ደጋግመን አስተውለናል፡፡

በኢትዮጵያ ስም ልዩነቶቻችንና ነባር ማንነቶቻችንን ሁሉ ደፍጣጭ ስለሆነው ዝንባሌና አዝማሚያ ጉዳይ በግልጽ መነጋገር መቻል አለብን፡፡ አንዱ ቡድን ራሱን እንደ አንድነት ባለ አደራና፣ የሁሉን አቀፍ ኢትዮጵያዊነት ብቸኛ ወኪል አድርጎ የመሰየሙ ጉዳይም ሌላው የአሳሳቢ ማንነትን መጎልበት የሚፈታተን ተግዳሮት ነው፡፡ በተራው ሌሎቹ ወገኖች እነሱን የሚመለከቷቸው በአንድ አካባቢ ወካይነታቸው እንጂ የልዕለ አገር ወካይነታቸው እንደማይዋጥላቸው አይገነዘቡም፡፡ በእኔ እይታ “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከነጋሺ መስተንግዶ እስከ ዜግነት መብት ተጋድሎ” በተሰኘው ምዕራፍ በዝርዝር የተመለከተትናቸው አግላይ አካሄዶችና ምን ክፋት አለው ዓይነቱ “ያለአዋቂ አፅናኝ” አለመግባባቶች በዚህ ሥር ይካተታሉ፡፡

             ዩሱፍ ያሲን 2009 ዓ.ም

ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት

Leave A Reply

Your email address will not be published.