ካነበብኩት: ኢትዮ -ጂቡቲ

(ሸጊት ከድሬ) – “ ጅቡቲ ነፃ በምትወጣበት ወቅት ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለመፈፀም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የነበረችበት ወቅት ነበር፡፡ የታላቋን ሶማሊያ አጀንዳ እውን ለማድረግ ያስችላል ተብሎ የተገመተው ይህ ወረራ የጅቡቲንም ነፃነት ሊጋፋ እንደሚችል እሙን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ላይ የነበራትን የይገባኛል ጥያቄ ከማለዘብ አልፋ በሂደት ጥያቄውን በጠቅላላ ያነሳች ቢሆንም በአብዛኛው በጅቡቲ አፋሮች ላይ የተመሰረተውን የነፃነት እንቅስቃሴ በመደገፍ የጅቡቲ ኢሳ ዜጎች ጥርጣሬ እንዲቀጥል አድርጋ ነበር፡፡ ስለሆነም ጅቡቲ ነፃ ስትወጣ ከጎረቤቶቿ የሚጠብቃት የፈረንሳይ ወታደር በአገሯ እንዲቀጥል አድርጋለች፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ህዝቡ አረብ ባይሆንም የአረብ ሊግ አባል ለመሆን ወስናለች፡፡ ጅቡቲ ስትቆረቆር ለኢትዮጵያ ወደብ ትሆናለች ተብሎና አብሮም የባቡር መስመር በተገነባበት እንኳን የተመሰረተች ነበረች፡፡ (በወቅቱ ኤርትራ በጣልያኖች ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡) እናም በኢትዮጵያና ጂቡቲ ወደብ መካከል በወደብ አገልግሎትና በባቡር መስመሩ ዙሪያ በተፈጠረ ትስስር በተነፃፃሪ ጠንካራ ሊባል የሚችል የኢኮኖሚ ትስስር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ኤርትራና ኢትዮጵያ በፌደሬሽን ከተዋሀዱበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ መጠቀሟን በእጅጉ መቀነሷ፣ የባቡር መስመሩም እየተዳከመ በመሄዱና በመጨረሻም በሲያድባሬ ወረራ ከጥቅም ውጪ በመሆኑ ትስስሩ በእጅጉ የላላበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ እናም ኢህአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ከጂቡቲ ጋር የነበረው ግንኙነት በፖለቲካ መስክ ለክፉ የማይሰጥ፣ በኢኮኖሚ መስክ ግን ደካማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ኤርትራ ነፃ ከወጣች በኋላም የጂቡቲ ወደብ አጠቃቀማችን በመጠኑ ቢጨምርም እስከ ድንበር ጦርነቱ ወቅት ድረስ በጣም ውስን ከመሆን የዘለለ አልነበረም፡፡

ከኤርትራ ወረራ በኋላ ግን ዋነኛው ወደባችን ጂቡቲ የሆነበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ በእጅጉ የተጠናከረበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ከጂቡቲ ጋር የሚያስተሳስሩ መንገዶች ተሻሽለዋል፣ ወደቡ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት ተካሂዶ እንዲሰፋ ተደርጓል፡፡ የቆየውን የባቡር መስመር ለማደስ የተደረገው ሙከራ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለት አዳዲስ መስመሮች እንዲዘረጉ እቅድ ተይዟል፡፡ በጂቡቲ በኩልም የታጁራን ወደብ በእጅጉ በማስፋት የምንጠቀምባቸውን ወደቦች ወደ ሁለት ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ የኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮችም እየተጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ትስስር በእጅጉ እየጠበቀ የመጣበት ሁኔታ ይታያል፡፡

ጅቡቲ ዋና ገቢዋ የወደብ አገልግሎት ከመሆኑ ጋር ተያይዞና የሻቢያ ጥቃት ሰለባም በመሆኗ የፖለቲካ ትስስሩም በመሰረቱ ጤናማና ጠንካራ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የዓለም አቀፍ አክራሪነትን ለመዋጋት የተሰለፈው የምዕራብ ኃይል ጂቡቲን እንደ መነሀሪያ በመውሰዱ በተለይም ከሶማሊያ የሚመነጨው የባህር ላይ ውንብድና እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የጂቡቲ መነሀሪያነት እያደገ በመምጣቱ ከዚህ የምታገኘው ገቢም አላት፡፡ ዞሮ ዞሮ መሰረቱ የተፈጥሮ ሀብት ኪራይ የሆነ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ሁሉ ጠንከር ብሎ ቢታይ የሚገርም አይሆንም፡፡ እናም ከወደብ አገልግሎት በሚገኘው ኪራይ ከኢትዮጵያም ጋር አልፎ አልፎ ልዩነቶች ቢከሰቱም በሞኖፖሊ ሁኔታቸው ለመጠቀም ቢሞክሩ የሚገርም አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የሚኖሩት ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው የጅቡቲና የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑ በሁለቱም ወገኖች በቂ ግንዛቤ የተያዘበት በመሆኑ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መሰረታዊ ጤንነትና ጥንካሬ ለአደጋ የሚጥል ነው ተብሎ የሚገመት ችግር አይታይም፡፡

ከጅቡቲ ጋር በየጊዜው የሚያጋጥሙ ልዩነቶች ባስቀመጥነው መርህ መሰረት እየፈታን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ከጂቡቲ ውጪ ያሉ ወደቦችን ለመጠቀም የምናደርገው ርብርብ የጂቡቲን ጥቅም ለመጉዳት በማሰብ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም የቆየውን የጂቡቲ ወደብን ብቻ ሳይሆን አዲሱን የታጁራን ወደብም ጭምር በላቀ ደረጃ መጠቀማችንን እንደምንቀጥል ልናረጋግጥላቸው ይገባናል፡፡ የኢትዮጵያ እድገት በሂደት ኢኮኖሚያችን በአንድና በሁለት ወደቦች ብቻ ሊስተናገድ የማይችል ስለሚያደርገው፣ የተለያዩ አገሮች ወደቦች ለተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ቅርበት ስላላቸው፣ የኢትዮጵያ እድገት ሁሉንም ጎረቤቶቻችንን በሚጠቅም መልኩ ለማንቀሳቀስ ስለሚያግዝ ኢትዮጵያ የተለያዩ አማራጮች ማግኘቷ አንዱን ትታ በሌላው ለመጠቀም ሳይሆን በሁሉም ግን ውድድር ባለበት ሁኔታ ለመጠቀም እንደሆነ ልናስረዳቸው ይገባል፡፡ እንደዚህ አይነቱ አሰራር የኢትዮጵያ ህዝብ በወደብ አልባነቱ የሚሰማውን ስጋት በማስወገድ ከሁሉም ጎረቤቶቹ ጋር በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር እንዲያግዘው፣ ይህ መሆኑ የጂቡቲንና የሌሎች ጎረቤቶችንም ጥቅም እንደሚስጠብቅ ልናስጨብጣቸው ይባል፡፡”

                                                             የኢትዮጰያ ህዳሴና ዓለማዊ ሁኔታ 2003ዓ.ም

Leave A Reply

Your email address will not be published.