ካነበብኩት

 

(ሸጊት ከድሬ) – “መዐህድ ከተመሰረተ ለአማራም ሆነ ለኢትዮጵያ ያከናወናቸው በጎ ተግባራት አላውቅም፡፡ ሩቅ ስለሆንኩ መሰለኝ፡፡ መዐህድ አሜሪካ በየቦታው አለ፡፡ ከ1984 ጀምሮ በአማራ ስም ቁጥር ሥፍር የሌለው ድግስ፣ ፓርቲ፣ ገንዘብ ማሰባሰቢያ (Fund Raising) ስብሰባዎች ያደርጋሉ፡፡ ብዙ ገንዘብ እንደተሰበሰበ አምናለሁ፡፡ ገንዘቡም ኢትዮጵያ ላለው አማራ ጉዳይ ውሏል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን ቀዝቀዝ ያለ መሰለኝ እንጂ ቀደም ሲል እዚህ አካባቢ ያለ ተፈላጊ ሸቀጥ (Hot commodity) አማራና ኦሮሞ ነበር፡፡ የትግሬዎቹ በድብቅ ስለሚመስል ብዙም አላወጉም፡፡ ብቻ በስማቸው መነገድ እንዳይሆን ብሎ እንዲያው ሰውነቱ ይፈራል፡፡

ሌሎች ሁለት ግልፅ ጉዳዮች አውቃለሁ፡፡ ቀኛዝማች ነቅአጥበብ የመዐህድ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ለአሜሪካ መንግስት የፍርድ ሚኒስቴር የስደተኞችና የዜጎች አገልግሎት (U.S department of justice, Immigration & Naturalization Service/INS) አንድ ደብዳቤ ፅፈው ኖሯል፡፡

እዚህ አሜሪካ ጥገኝነት ከየትም አገር የሚመጣ እንደየአገሩ ሁኔታ ለጥገኝነት የሚያበቃ የታሪክ ማስረጃዎች ያቀርባል፡፡ ከኢትዮጵያም የሚመጡ እንደዘመኑ አገራቸውን ጥለው የወጡበትን ምክንያትና መረጃ ያቀርባሉ፡፡ ታሰርኩ፣ ተገረፍኩ፣ ተሰደድኩ፣ በሃይማኖቴ፣ በፖለቲካ እምነቴ፣ ብሔረሰብ… የሚልና የመሳሰለ፡፡

የቀኛዝማችን ደብዳቤ ያየሁ ዕለት እንዲህ ሆነ፡፡ አንዲት ሴት ጥገኝነት ጠይቃ ላስተረጉምላት አብረን ወደ ተጠቀሰው መንግስታዊ አካል ሄድን፡፡ አማራ ነች፡፡ ያውም ደብረብርሃን፤ የመዐህድ አባል መሆኗን የሚያሳይ ማስረጃም አቅርባለች፡፡

አንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ የወሰደ ቃለ መጠይቅ (Interview) አደረግን፡፡ በመጨረሻም ጠያቂዋ ሴት “እርግጥ የመዐህድ አባል ነሽ?” “አዎ” በዚህ አለቀና “ትንሽ ጠብቁኝ” ብላ ወደሌላ ቢሮ ሄዳ አንድ ደብዳቤ ይዛ መጥታ አንብብ ብላ ሰጠችኝ፡፡ የቀኛዝማች ነቅአጥበብ ሁለት ገፅ ሙሉ በእንግሊዝኛ የተፃፈ ደብዳቤ፡፡

ደብዳቤው በአጭሩ የሚለው “..አማራ ነኝ፤ የአማራ ድርጅት አባል ነኝ የሚል ማስረጃ አትቀበሉ፡፡ እኛ አባላት የለንም፡፡ መታወቂያ ሰጥተን አናውቅመ፡፡ የድጋፍ ደብዳቤ ፅፈንም አናውቅም” የሚል ነበር፡፡

እኔ ደነገጥኩ፡፡ አዘንኩ፡፡ መደንገጤ የዚህች አንዲት ምስኪን ኢትዮጵያዊት ጉዳይ ጨንግፎ ከአገር ያስወጧታል በሚል ነው፡፡ ማዘኔ፣ ቀኛዝማችም ሆነ ማንም ቀና ልቦና ያለው ሰው እንዲህ ያለ ቋሚ ግን ጎጂ መርዘኛ ደብዳቤ ለአሜሪካ መንግስት እንዴትስ ይፅፋል በሚል ነበር፡፡ እንኳንስ አማራ ሶማሌ፣ ትግሬ፣ ኤርትራዊ፣ አፋር፣ እንዲያውም ከተሳካላት ማንስ ቢሆን የመአህድ አባል ነኝ ቢል ጥገኝነት ቢያገኝ ቀኛዝማች ምናቸውስ ተነካ ምናቸው ተጎዳ ሰው ቢጨንቀው ያልፍልኝ እንደሁ ብሎ አይደል አገሩን ጥሎ የሚሰደድ እንዴት ለሰው ዘር በጎነት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እታገላለሁ የሚል ድርጅት መሪ ይህን ሰፋ ያለውን “ የጋራ ቤታችንን” ምስል (The Big Picture)ይስተዋል ብዬ አዘንኩ፡፡ ወይስ ያልተነገረ ወይ ተነግሮ እኔ የሳትኩት ነገር ይሆራል?

ኢንተርቪው አድራጊዋም ገርሟት ነበር፡፡ “እንዴት አባል የሌለው ድርጅት ይሆራል” አለች፡፡ “ለአንቺ ጉዳይ እኔ ይህንን ደብዳቤ ከግምት ላስገባ እወስናለሁ” አለች፡፡ ለሴትየዋም በ3ኛው ሣምንት ጥገኝነቱ ተፈቀደላት፡፡”

የትዝታ ፈለግ

አሰፋ ጫቦ (2006)

Leave A Reply

Your email address will not be published.