“ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና አንድነት”

ካነበብኩት

(ሸጊት ከድሬ) – በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና መልዕክዓ ምድራዊ አስፋፈር በአንፃራዊነት ታሪካዊ ልዩነት ያላቸው ህዝቦች ከማንነታቸው ጋር በተያያዘ ራሳቸውን የሚገልፁ እስከሆነ ድረስ፣ በዛ አገር ውስጥ በማንነት ላይ የተመሠረተ ብዝሃነት የሰፈነበት አገር ይባላል፡፡

ከብዝሃነት፣ ከፍትሃዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በዓለማችን ለቁጥር የሚታክቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡አንዳንዶቹ አገራት ፈጥነው ድህነትንና ኋላቀርነትን በማስወገድ እንዲሁም በህዝቦቹ ዘንድ መከባበር ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲዊ አንድነት በመገንባት ችግሮቹን እየፈቱ ይሄዳሉ፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ አገራት ደግሞ ከቆየው ድህነትና ኋላቀርነት ሁኔታቸው በተጨማሪ፣ በአገራቸው የሰፈነው ከማንነት ጋር የተያያዘ ብዝሃነት የእድገታቸው፣ የውበታቸውና የእውነተኛ ማንነታቸው መገለጫ መሆኑ ቀርቶ የአለመግባባትና የግጭት ምክንያት ይሆናል፡፡ አንዳንዶቹ እንደ ዩጎዝላቢያ አይነቶቹ አገሮች እስከ መበታተን ደርሰዋል፡፡ በአንዳንዶቹ እያሰለሰ የሚያገረሽ በሽታ ሆኖ በማንነት ላይ የተመሠረተ ግጭት መገለጫዎች ሆነው ይታያሉ፡፡

ከማንነት ጋር የተያያዘ ብዝሀነት በሰፈነባቸው አገራት፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ትክክለኛውና ብቸኛቸው አማራጭ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የቋንቋ፣ የባህል፣ የስነ-ልቦና፣ የኃይማኖትና ተጓዳኝ ልዩነቶች አሉን ብለው የሚያምኑ በአንድ አገር የሚኖሩ ህዝቦችን አስማምቶ ማልማትና ማሳደግ የሚችል ብቸኛ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አማራጭ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከማንነት ጋር የተያያዘ ብዝሃነት በሌለባቸው አገራት እንደ ሀሳብ ሊነሳ አይችልም፡፡ አንድ ብሔርና አንድ ሃይማኖት ሰፍኖ በሚታይባቸው አገራት የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ሊነሳ አይችልም፡፡ የደቡብ ኮሪያን ህዝብ እንደ ምሳሌ ወስደን ብንመለከት፣ ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነው አንድ ቋንቋ የሚናገርና በሃይማኖት ረገድም ቢሆን ብዙ ተፎካካሪ እምነቶች ጐልተው የማይታዩበት አገር በመሆኑ፣ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ጣራ ላይ ቢደርስም፣ በእብሪት እየተነሳሱ ከጐረቤት አገራት ጋር ከመነታረክ ጣጣ ይመጣ እንደሆነ እንጂ፣ በአገር ውስጥ የሚያስከትለው ከአንድነት መናጋት ጋር የተያያዘ ጉዳት ከባድ አይሆንም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከማንኛውም አይነት ብሔርተኝነት ይለያል፡፡ የትምክህተኛ አስተሳሰብ አንዱን ቋንቋ፣ ባህልና ኃይማኖት ከፍ አድርጐ ሌላውን ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት አሳንሶ ይመለከታል፡፡ በብዝሃነት የሚገለፀው ማንነት በተበራከተበት አገር የትምክህተኛ አማራጭ እየናኘ ሲሃድ፣ በዚሁ ትይዩ “እየተገፋን ነው” ብለው የሚያስቡ ህዝቦች አሜን ብለው ስለማይቀበሉ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህዝብንና አገርን የሚበትን አደገኛ በሽታ ነው፡፡

በትምክህት አስተሳሰብ ትይዩ ሊሰፍን የሚችለው ደግሞ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ትምክህተኝነት የሚፈጥርበትን የግፊት ኃይል እንደዋነኛ ሰበብ አድርጐ፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ትምክህትን መዋጋት ሲገባው፣ ራሱን ማግለልንና መነጠልን በመምረጥ “እወክልሀለሁ” የሚለው ብሔር ገዥ ለመሆን መንቀሳቀስን ያስቀድማል፡፡

ይህ አማራጭም ቢሆን ማንነቱ እንዲከበርለት የጠየቀን ህዝብ ስሜት ለአልባሌ ተግባር ከማዋል ያለፈ፣ በመፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ ሊገነባ የሚችለውን ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ከአንድነቱ ሊገኝ የሚችለውን የጋራ ተጠቃሚነት የሚጐዳ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ አስተሳሰብና ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም የትምክህተኛም ሆነ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰቦች ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍፁም ተቃራኒ እና ለህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነትም የማይበጁ የዴሞክራሲያዊ አንድነት ነቀርሳዎች ናቸው፡፡

የትምክህተኛም ሆነ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰቦች ለዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍፁም ተቃራኒዎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ሊገኝ የሚችለውን ህዝባዊ ተጠቃሚነት የሚያሳጡ “እንወክልሀለን ” ለሚሉትም ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ሊያጐናፀፉ የማይችሉ ፀረ-ዴሞክራሲ አማራጮች ናቸው፡፡ የትምክህተኛ አስተሳሰብ አማራጭ ይዘው የሚቀርቡ ኃይሎች፣ “እንወክልሐለን” በሚሉት ህዝብ ስም የሚምሉና የሚገዘቱ ቢሆኑም፣ ለህዝቡ ትርጉም ያለው ለውጥ ሲያመጡ አልታዩም፡፡ ሊያመጡም አይችሉም፡፡

የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ትግበራ እንቅፋቶች አሉት፡፡ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሰረታዊ እንቅፋቶች በአስተሳሰብና በአፈፃፀም ደረጃ የሚስተዋሉ ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ከአስተሳሰብ አኳያ ዘወትር የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን አስተሳሰብ ከተቃራኒው አመለካከት እየለዩና የአስተሳሰብ ጥራትን እያዳበሩ መሄድ ካልተቻለ፣ በንግግር ብቻ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እያሉ በሰመመን በትምክህት ወይም በጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቆ መገኘትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም ዘወትር በመሪዎች፣ በፈፃሚዎችና በጠቅላላ ህዝቦች ውስጥ የሚታየውን የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ከተቃራኒው አስተሳሰብ ጋር በንፅፅር ይዞ ትክክለኛውን አስተሳሰብ በአግባቡ እያጠሩ ያለመሄድ ችግር አንዱ እንቅፋት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት አስተሳሰብን ለማስረፅ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆነው የብሔርተኝነት አስተሳሰብ መደፈቅ ይኖርበታል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ባልሰፈነበትና ጥልቀት ባላገኘበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ሊያድግና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሊገነባ አይችልም፡፡ እነዚህን የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲና የአብሮነት እንቅፋት የሆኑ ኋላቀር አስተሳሰቦች በድፍረት ለመጋፈጥ ቁርጠኛ የሆነ አመራር በየደረጃውና በየተቋማቱ መበራከትና መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በብሔር ካባ የተሸፈነና በዴሞክራሲ አግባብ ያልተገራ ብሔርተኝነት በነገሰበት ሁኔታ የዴሞክራሲያዊ አንድነትን ዘር ዘርቶ ማብቀልና ማሳደግ ከባድ ይሆናል፡፡

ከማንነት ጋር የተያያዘ ብዝሃነት በሰፈነበት አገር፣ ሁለተኛው እንቀፋት ከተግባራዊ አፈፃፀም ጋር የተያያዘው ችግር ነው፡፡ የቋንቋ፣ የባህል፣ የኃይማኖትና የስነ-ልቦና ብዝሀነት በሰፈነበት ሁኔታ ፣ አንዱ ከሌላው በልጦ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ ከሆነ ወይም ደግሞ ህዝቦቹ አንዱ የበለጠ ተጠቅሟል ብለው ካመኑ የአንደኛው ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት በመንግስት ድጋፍ እያደገና የበለጠ የተስፋፋ ከመሰላቸው ማህራዊ ውጥረትን የማስከተል እድሉ ሰፊ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በሌሎች ማንነታቸው እየተጣሰ ከመሰላቸው ወይም በአግባቡ ድጋፍ ካልተደረገላቸው በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ቅሬታና አለመግባባት ብሎም ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል፡፡

ጠቅለል ባለው አገላለፅ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንቅፋቶች ከላይ የተጠቀሱት የአስተሳሰብና የአፈፃፀም ችግሮች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከእነዚህ ጋር የሚያያዙም ሆኑ ራሳቸውን ችለው የሚታዩ ቀጣይነት ያላቸው የልማትና ዴሞክራሲ አደረጃጀቶችንና ተቋማትን የማሳደግ ጉዳይ ቁልፍ ስፍራ ይይዛል፡፡ ፈጣን ልማት እየተረጋገጠና ከዚሁ ፈጣን ልማት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ፣ የተስፋ ብርሀን ጐልቶ እየታየው ካልሄደ ከምትገነው ትንሽ ነገር አንዱ ብሔር የተሻለ ተጠቃሚ ሆኗል ብሎ በማመን መናጨትና መጋጨት ሊያጋጥም ይችላል፡፡

እንቅፋቶቹን ከማስወገድ አኳያ በአስተሳሰብና በአፈፃፀም ፍትሀዊነትን ማስፈን ይገባል፡፡ ፍትሃዊነት ሲባል የተገኘችን ትንሽ ነገር በፍትሃዊነት ማካፈል ብቻ ሳይሆን፣ ትልቅ ሀብት ፈጥሮ በትልቁ ለመካፈል ቀን ከሌት መትጋትን ይጠይቃል፡፡ የዚህ ትጋትና ተነሳሽነት ምንጭ ሊሆን የሚችለው ደግሞ “ ድህነትና ኋላቀርነት በአዝጋሚ እድገት የህዝቦችንና የአገርን አንድነት አደጋ ላይ ይጥላሉ” ከሚል ጥልቅ መሰረተ ሀሳብ በመነሳት ሲታይ ብቻ ነው፡፡

ያልተማከለን አስተዳደር ማዕከል አድርገው ሂደቱን በገበያ ሥርዓቱ የመሩ አገራት ያልተማከለ አስተዳደር በሚሰጠው የውስጥ ነፃነት፣ ህዝቦች የሚፈጥሩት መረጋጋትና የእኩዮሽ መንፈስ ለሁለንተናዊ ለውጥ አቅም ሲሆን ታይቷል፡፡ ይህንኑ ሁኔታ ልማታዊ በሆነ የገበያ ሥርዓት፣ እያጠናከሩ በሄዱ ቁጥር ፈጣን ልማት እየተረጋገጠ እንዲሄድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ፈጣን ልማት በመጣ ቁጥር በማንነት ላይ የተመሠረተው መፈላለግ እየቀነሰ፣ በምትኩ በገበያና በኢኮኖሚ ጥቅም ላይ የተመሠረተው መፈላለግ እየተጠናከረ እንዲሄድ እድል ይሰጣል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና በኢትዮጵያ ሁኔታም ጅምር ሂደቱ የሚያሳየው በዴሞክራሲያዊ የውይይት መድረኮች፣ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን የማጐልበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በትምህርት ቤት፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙሃን አውታሮች፣ በመከላከያ ሠራዊትና በመንግስታዊ ተቋማት፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ የዴሞክራሲ ተቋማት በመከባበር፣ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ብሎም ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍን የተቀነባበረ ስራ መስራት ይጠይቃቸዋል፡፡

እነዚህ ጣምራ ጥረቶች በታቀደ አግባብ ተግባራዊ ከተደረጉ፣ ማንነትና ከማንነት ጋር የተያያዘው ብዝሃነት መረገም ሳይሆን፣ መታደል ይሆናል፡፡ ያለመግባባትና የግጭት ምንጭ ሳይሆን የእድገት፣ የብልፅግናና የውበት ምንጭና መገለጫም ይሆናል፡፡ ለዚህም ፍቱን መድኃኒቱ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታን ማስፈን፣ ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት፣ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ሁነኛ መፍትሔ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች በአግባቡና በተሟላ ህዝባዊ ወገንተኝነት እንዲሁም በዓላማ ፅናት መንፈስ በመፈፀምና የህዳሴውን ጉዞ በማፋጠን ሊረጋገጥ የሚችል ነው፡፡

(አለምነው መኮንን 2009 ዓ.ም)

ፖለቲካ ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ ሕዳሴ

Leave A Reply

Your email address will not be published.