ካነበብኩት

(ሸጊት-ከድሬ)

“… የሃሳብ ድሆች መሆናችን በብዙ መንገዶች ይገለፃል፡፡ አንዳንድ ምሣሌዎችን እንጥቀስ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ምዕተ ዓመታት የሥነ-ጽሑፍ ባለቤት ቢሆንም በመሃይምነት ግርዶሽ ውስጥ ከሚኖሩ ህዝቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ መሃይምነት ደግሞ ከሁሉም በላይ የሃሳብ ድህነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ መደበኛ ግብርና፣ የዕደ-ጥበብ ሙያ፣ ሥነ -ጽሑፍ፣ ሥነ-መንግስትና መለኮታዊ ኃይማኖት ከፈጠሩ ጥንታዊ ህዝቦች መካከል ቀደሚውን ሥፍራ ይዛለች፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ በጀመረቻቸው የዕውቀት፣ የምርት የድርጅትና የኃይማኖት መሠረት ላይ በተከታታይ በመገንባት ፋንታ መሠረቱን እየናደች የሄደች አገር ናት፡፡ ለምሳሌ የዕውቀትና የጥበብ ምንጭ የሆኑትን የኃይማኖት ተመራማሪዎች፣ ደብተራዎችና የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ስታሳድድ የኖረች አገር ናት፡፡ ቤተ-መንግስትም ቢሆን ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፀረ-ምሁር አቋም ይዞ ነው የተጓዘው፡፡ ከዚህ የበለጠ የሃሳብ ድህነት ከየት ይምጣ?

የኢትዮጵያ ህዝብ የድህነቱ ምንጭ ስልተ ምርቱና ማኀበራዊ ሥርዓቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ስልተ ምርትም በመደበኛ ኋላቀር እርሻና በዘላንነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሁለቱን ስልተ ምርቶች ለመለወጥ ህዝቡ የሚያደርገው ጉልህ ጥረት አይታይም፡፡ ይህም የሃሳብ ድህነት አንዱ ገጽታ ነው፡፡

ሰው እንደመሬት ነው ይባላል፡፡ መሬት በውስጥዋም በላይዋም ብዙ ሃብት ይዛለች፡፡ ካልሰሩባት ግን ጦም ታሳድራለች፡፡ ከሰሩባት ታስከብራለች፡፡ ሰውም እንዲሁ ነው፡፡ በውስጡ ያለውን ኃይል በዕውቀት ፈልፈሎ ካላወጣ በስተቀር ለቁም ነገር አይበቃም፡፡ እኛ የሚቀናን ራሳችንን መመርመርና ድክመታችንን ማረም ሳይሆን በሌላው ላይ ጣታችንን መቀሰር ነው፡፡ አሁን አሁን በተያዘው ዓይነት ለኦሮሞ ኋላቀርነት አማራን፣ ለአማራ ኋላቀርነት ትግሬን፣ ለትግሬ ኋላቀርነት አማራን፣ ወዘተ. እየወቀስን መኖር ጀምረናል፡፡ የእያንዳንዱ ኋላቀርነት በቅድሚያ ከራሱ የሚመነጭ መሆኑን ግን ለማየት አንፈልግም፡፡ የሃሳብ ድህነት ሌላው ገጽታም ይህ ነው፡፡

የሽግግር መንግስት ከተመሠረተ በኋላ እንደተጨቆኑ በአፅንኦት ይገልጹ ከነበሩት ብሔሰቦች ተወካዮች መካከል የአማራ፣ የኦሮሞና የትግሬ ህዝብ ተወካዮች ነበሩ፡፡ እነርሱን ማን እንደጨቆናቸው ግን በግልጽ አያስቀምጡም ነበር፡፡ የነፍጠኛው ሥርዓት ጨቆነን ቢሉ እንኳን የዚያም ሥርዓት ግንባር ቀደም ባለቤቶቹ ሦስቱም ብሔረሰቦች እንደነበሩ ማብራራት አይወዱም በሃሳብ ድህነት ምክንያት፡፡”

ዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካል በ1993 ለ “እፎይታ” ጋዜጣ ከሰጡት ቃለመጠይቅ የተወሰደ

1 Comment
  1. Solomon says

    Dear Ben,

    I just heard the great historian Richard Pankhurst has died. I was very sorry to hear this as he had devoted his life to researching Ethiopian history. I do hope he will be given a fitting send off at Sellasie Cathedral with our Ethiopian greats. Please cover this sad news in your website.

Leave A Reply

Your email address will not be published.