ውሺ ቁጥር አንድ የተባለ የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ሊሰማራ ነው

(ኢዜአ)- ውሺ ቁጥር አንድ የተባለው የቻይና ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያ በድሬድዋ የተቀናጀ የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በኩባንያው ኃላፊዎች በቻይና ውሺ ከተማ ተደርጓል።

ኩባንያው በሚያቋቁመው ፋብሪካ ክርና ጨርቃ-ጨርቅ እንደሚያመርት ታውቋል።

ድርጅቱ ከ100 አመት በላይ በዘርፉ ልምድ ያለው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በዓመት ከ26 ሺ በላይ ቶን ክርና ከ30 ሚሊዮን ሜትር በላይ ጨርቅ እያመረተ ይገኛል።

ይህን ምርት 75 በመቶ የሚሆነውን ወደ አውሮፓ፤ አሜሪካ፤ ጃፓንና ኮሪያ እንዲሁም የደቡብ ኤዥያ አገራት ያቀርባል።

ድርጅቱ ይህንኑ ልምድና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የገበያ ትስስር ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት አገሪቱን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንቨስትመንቱ አገሪቷን ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ማዕከል ያደረገ፣ ዘላቂና የተቀናጀ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።

የውሺ ከተማ ከንቲባ ዋንግ ኩዓን በበኩላቸው የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ድጋፋቸውን አጠናክረው አንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንቱ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማስገኘቱ ባለፈ በሚፈጥረው የተቀናጀ የእሴት ሰንሰለት ብዙዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በዋናነት ጥጥና መሰል ግብዓቶችን ከአገር ውስጥ መግዛትና በፋብሪካ በማምረት ለአገር ውስጥ የጥጥ አምራቾች የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል።

መቀመጫውን የቻይናዋ ጂያንሱ ውሺ ከተማ ያደረገው ውሺ ቁጥር አንድ ግዙፍ የጨርቃጨርቅ አምራች ኩባንያ ከ100 ዓመት በላይ ልምድ ያለው፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም  የካበተ ልምድ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋታል ተብሏል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.