የሀውዜን ሰማዕታት የማንነታችን እና የነጻነታችን መሰረቶችን ናቸው :-ጠ/ሚ ዶክተር አቢይ አህመድ

(EBC)- የሀውዜን ሰማዕታት የማንነታችን እና የነጻነታችን መሰረቶችን ናቸው ሲሉ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የሃውዚን ሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን መሰረት በማድረግ ባስተላለፈት መልእክት ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሀውዜን ለተፈጸመው ጭፍጨፋ መታሰብያ አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል።

የመልእክቱ ሙሉ ይዘት

በምስራቃዊ ትግራይ ትንሽ ከተማ በሀውዜን እንደሁሌውም የነጋችው የእለተ ረቡእ ጀምበር እንደሁልጊዜው ሆና አላለፈችም፡፡ ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሰአት ገደማ የሀውዜንን ሰማይ ይዞር ነበረው የሞት ጥላ 2ሺ500 ንጹኀን ዜጎችን እንደወጡ ካስቀራቸው ይሄው ድፍን 30 አመት ሞላው፡፡

የእነዚህ ንጹሀን ወገኖቻችን እልቂት እሩብ ምእተ አመትን መሻገሩ እውን ቢሆንም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ህመሙን እና ሀዘኑን የዛሬ ያህል እየታመመ፣ የአሁን ያህል እያዘነ እና ለሁልጊዜውም እየዘከረ ዛሬ ደርሰናል፡፡

ለዛሬ ሀገራዊ አንድነታችን እና ኢትዮጵያዊ ህልውናችን ትላንት መሰረት ናት ስንል በሀውዜን የተሰዉት ኢትዮጵያውያን የማንነታችን እና የነጻነታችን መሰረቶች ናቸው ማለት እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይደለም፡፡

መንግስት የህዝቡ ጥላ፣ ጠባቂ፣ አዳኝ እና የክፉ ጊዜ ከለላ ነው ከሚለው እሳቤ በፍጹም ተቃርኖ በሚገለጽ ጭካኔ እና አረመኔያዊ ድርጊት በመንግስታቸው የተጨፈጨፉት ውድ ዜጎቻችን ለትላንነታችን ጸጸት ለነጋችን ደግሞ ትምህርት ሆነው ለዘለአለሙ ቢያሸልቡም በኢትዮጵያችን ታሪክ እና በህዝባችንም የክብር ልክ ውስጥ ሁሌም የምናነግሳቸው- መቼም የምናስባቸው ጀግኖቻችን ናቸው፡፡

የዚህች ሀገር ደግ ቀን እንዲነጋ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እና በገዛ መንግስታቸውም ጭምር በእሳት አረር የቀለጡ በጭካኔ በትርም የተቀጠቀጡ እልፍ ሰማእታት ያሉን ህዝቦች ብንሆንም እነዚህን ባለውለታዎቻችንን አስታውሰን ከማመስገን፣ ከመዘከር እና በታሪካችን ማህደር ውስጥም ተገቢውን የክብር ስፍራ ከመስጠት አንጻር አሁንም ብዙ ይቀረናል፡፡

ከሀውዜን ሰማይ ላይ እሳት ዘንቦባቸው በሀውዜን ምድር ላይ አመድ ያደረጋቸውን ወገኖቻችንን እና በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የጨካኞች መዳፍ ህይወታቸውን የነጠቃቸውን ወገኖቻችንን ይበልጥ ከማክበር፣ ከመዘከር እና ታሪካቸውን ከመከተብ ረገድ ሁሉም ዜጋ በተገቢው መንገድ የቤት ስራውን እንዲሰራ ጥሪዬን እያቀረብኩ መንግስትም ሰማእቶቻችንን በተገቢው ክብር ከፍ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

በሀውዜን በነበረው ዘግናኝ እልቂት የተፈጸመው ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ በትላንት ታሪክነቱ አስበነው የምናልፈው ብቻ ሳይሆን ዛሬ እና ነገም ይሄ እንዳይደገም ከራስ ጋር እንደሚገባ ቃልኪዳንም የምንቆጥረው ክቡር መስዋእትነት ነው፡፡

በዚያ የእልቂት እና የጥፋት ማእበል ውስጥ 2500 ወገኖቻችን በገዛ መንግስታቸው በአንዲት ጀምበር እንደዋዛ ከማለቃቸውም ባሻገር ከ600 በላይ የሚሆኑ አስከሬኖች በአንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ መደረጋቸው ሀዘናችንን እጥፍ ድርብ አድርጎት ልባችንን ሰብሮታል፡፡

ከረፋዱ 5 ሰአት እስከ አመሻሹ 11 ድረስ በዘለቀው እና 6 ሰአታትን ላስቆጠረው የሀውዜን የጥፋት መልእክት የተመደቡት 6 ወታደራዊ የጦር ሚጎች የመስቀል ቅርጽ እየሰሩ የሀውዜንን ሰማይ ሲናኙበትና ሞት ያንን ምድር ሲዞረው፤ ንጹሁ የሀገሬው ሰው ግና ገና መሞቅ የጀመረ ገበያ ላይ ነበር ቀልቡ እና ልቡ የነበረው፡፡ ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ለገጠማቸው እና አሰቃቂ በሆነ መልኩ ክፉ ጥፋት ለጎበኛቸው የሀውዜን ወገኖቻችን ፍቅራችን እና ክብራችን ወሰን የሌለው ቢሆንም ሀዘኑ ግን የሁልጊዜያችንም ነው፡፡

መንግስት ካለፈው ታሪክ ተምሮ እና የነገውንም ደግ ቀን በደግ እይታ አሻግሮ ትላንት የገጠመን መአት ከእንግዲህ እንዳይገጥመን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ በዚህ ታሪካዊ ቀን ላይ ቆሞ እንደገና ቃል ኪዳኑን ያድሳል፡፡ ያሰብነው ሁሉ የሚሳካው እና ከመጠፋፋት አዙሪት ወጥተን መልካም ሀሳባችን ፍሬ የሚያፈራው ህዝባችን ከመንግስት ጎን ቆሞ ጥሩውን በመደገፍ እና ልክ ያልሆነውንም በምክንያት በመንቀፍ መደጋገፍ ሲቻል በመሆኑ ሁላችንም በዚሁ አግባብ እንቆም ዘንድ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በዚያ ክፉ ቀን በንጹሀን ወገኖቼ ላይ በደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋም ሁሌም የሚሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እና የልብ ስብራት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!” “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ” ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

Leave A Reply

Your email address will not be published.