የሀገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ የኢህአዴግን ምላሽ ለመስማት ቀጠሮ በመያዝ ተለያዩ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- በፀረ ሽብር ህጉ ላይ እየተደራደሩ ያሉት ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢህአዴግን ምላሽ ለመስማት ቀጠሮ በመያዝ ተለያዩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአዋጁ ላይ ሊሻሻሉ፣ ሊሰረዙ እና ሊጨመሩ ይገባል ብለው በፅሁፍ ያዘጋጁትን የድርድር ሀሳብ አስረድተዋል።

በሃሳባቸውም የፀረ ሽብር ህግ ለሃገሪቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ሆኖም የ11ዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ፣ መኢብን፣ የገዳ ስርዓት እና መኦዴፓ አዋጁ ከህግ መንግስቱን የሚፃረሩ ህጎችን የያዘ በመሆኑ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ነው በድርድር ያነሱት።

ኢራፓ አዋጁ ሙሉ በሙሉ በሌላ መተካት አለበት በማለት የድርድር ሀሳብ አቅርቧል።

ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ለተነሱ የድርድር ሀሳቦች በፓርቲው በኩል ያለውን ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ለቀጣይ ሳምንት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዘዋል።

ፓርቲዎቹ እንዲሻሻሉና እንዲብራሩ ከጠየቁት

  • የፀረ ሽብር ህጉ የሀገሪቱን ህገ መንግስትና አገሪቱ የፈረመቻቸውን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚጣረስ ነው
  • ሽብር ለሚለው ቃል ግልፅ ትርጓሜ ሊቀመጥ ይገባል
  • ተመጣጣኝ እርምጃ ሲባል እስከምን ድረስ ነው?
  • ማሰብ፣ ማቀድና ማሴር ስላልተፈፀሙ በወንጀል ሊያስጠይቁ አይገባም
  • ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ብርበራ እና እስር መፍቀዱ ተገቢ አይደለም
  •  በፀረ ሽብር ህጉ ከተከሰሱ ግለሰቦች ጋር መገናኘት ማስጠየቁ ተገቢ አይደለም፣
  • በየአንቀፆቹ “ እና ሌሎች” ተብለው የተጠቀሱ ጉዳዮች አከራካሪ ናቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በተያያዘም ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ ይፈታሉ የተባሉ እስረኞች ሂደት በምን ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ኢህአዴግ አዳራዳሪዎች በሚያወጡት የጊዜ ሰሌዳ ለተደራዳሪ ፓርቲዎች ማብራሪያ እስጣለው ብሏል።

ኢህአዴግ በጊዜ እጥረት ምክንያት በቀረቡ ሃሳቦች ላይ መልስ ባለመስጠቱ፤ በቀጣይ የድርድር  ጊዜ ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ይዞ እንደሚቀርብ  አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ስለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ኢህአዴግ ጥያቄውን መቀበሉን ገልጿል።

ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም በታህሳስ 10 እና 13 ቀን 2010 ዓ.ም ያደረጓቸው ድርድሮችን ቃለ ጉባኤም አፅድቀዋል።

በአዋጁ ላይ ተጨማሪ ድርድር ለማካሄድ ለጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.