የህዝቡን ሰላም ለማወክ ከሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ሀይሎች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ኦህዴድ አሳሰበ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የህዝቡን ሰላም ለማወክ ከሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ሀይሎች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አሳሰበ።

በኦሮሚያ ክልል በሚስተዋለው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ዙሪያ የኦህዴድ ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ትናንት ምሽት ውይይት ማካሄዳቸውን የክልሉ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።

በዚሁ ውይይትም ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት፥ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተሃድሶ አመራሩ አማካኝነት የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በአሁኑ ጊዜ በጀመረው ስራ የህዝቡን ጥቅም ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረገ መሆኑንም ነው የገለፁት።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ መንግስት እየተሰራ ያለው ስራ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ እንዲሁም አንድነትን እያጠናከረ መምጣቱን አስታውቀዋል።

አሁን የተጀመረው ትግል እና ስራ የኦሮሞን ህዝብ ያስደሰተ ቢሆንም የህዝቡን ሰላም የማይወዱ አፍራሽ ሀይሎችን ግን አስደንግጧል ያሉት ዶክተር አብይ፥ እነዚህ አፍራሽ ሀይሎች የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የተጀመሩ ስራዎችን ለማክሸፍ ከመንቀሳቀስ አልቦዘኑም ብለዋል።

እነዚህ አፍራሽ ሀይሎች ለመጠቀም እየሞከሩት ካለው ዘዴዎች ውስጥም ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የቆሙ በማስመሰል ወጣቱን በስሜት በማነሳሳት ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት አንዱ መሆኑን ዶክተር አብይ ተናግረዋል።

በዚህ መልኩ በትናንትናው እለት በሻሸመኔ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ያስታወቁት ዶክተር አብይ፥ ከ30 በላይ ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ነው ያስታወቁት።

እንዲሁም በምእራብ ሀረርጌ ዞን ቦኬ ወረዳ በተካሄደ ሰልፍም የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ሶስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውንም ዶክተር አብይ ገልጸዋል።

በዚህ ሰልፍ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል ያሉት ዶክተር አብይ፥ የክልሉ መንግስት ይህንን ህገ ወጥ ተግባር የፈፀሙ አካላትን በመከታተል ለህግ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።

የተጎጂ ቤተሰቦችን በኦሮሞ ባህል መሰረት ከጎናቸው በመቆም አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋልም ብለዋል።

የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ አክለውም፥ የክልሉ ወጣቶች ስሜታዊ በማድረግ ወደ አላስፈላጊ ሰልፎች ከሚገፋፏቸው አካላት ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ህዝብ እና የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች የክልሉ ሰላም እና አንድነት እንዲጠበቅ ከፍተኛውን ሚና መጫወት አለባቸው ያሉት ዶክተር አብይ፥ ወጣቶችም በጥፋት ሀይሎች አጀንዳ እንዳይታለሉ መምከር አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.