የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

(ኢዜአ)- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራል መንግስት የሚውል የ14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ጥር 15 ቀን 2010 ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል መንግስት የ2010  ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅን ለበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወቃል።

በዛሬው እለትም 13ኛ መደበኛ ስብሰባውም የቋሚ ኮሚቴውን ውሳኔ መርምሮ ለፌደራል መንግስት 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀትን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ለ2010 በጀት ዓመት ካጸደቀው 320 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጠቅላላ የወጪ በጀት ውስጥ ተይዞ የነበረው የ2 በመቶ መጠባበቂያ በተለያዩ አካባቢዎቸ የደረሰውን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል አገልግሎት ላይ በመዋሉ ተጨማሪ በጀቱ አስፈልጓል።

የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ታደሰ ሪፖርት በአቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከጸደቀው ተጨማሪ በጀት ውስጥ አንድ ቢሊዮኑ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲሁም 500 ሚሊዮኑ የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የመቀበል አቅምን ለማጠናከር ይውላል።

ለአገሪቱ የዲጂታል ቴሌቪዥን ማስፋፊያ የመሳሪያ ግዥ ቀሪ ክፍያ ለመፈጸም ከተጨማሪ በጀቱ ውስጥ 300 ሚሊዮን እንደተመደበለትም ገልጸዋል።

በተጨማሪ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመደገፍ 5 ቢሊዮን ብር፤ ቀሪው 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደግሞ በ2010 በጀት ዓመት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እጥረት ላጋጠማቸው አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በመጠባበቂያነት የተያዘ መሆኑን ታውቋል።

የወጪ በጀት አሸፋፈኑ በተመለከተ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮኑ ባንኮች ካገኙት ‘የነፋስ አመጣሽ ገቢ’ ግብር የሚሰበሰብ ሲሆን፤ ቀሪው ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ እንደሚገኝ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.