የመተማ ዮሐንስ የደረቅ ወደብ ግንባታ ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

(ኢዜአ)- የመተማ ዮሐንስ ከተማን የደረቅ ወደብ ግንባታ ለማስጀመር የተነሺዎች የካሳ ግምት ጥናት ተጠናቆ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተወካይ አቶ አድኖ አያናው እንደገለፁት በከተማው ለደረቅ ወደብ ግንባታ የሚውል 44 ሄክታር መሬት በጥናት የመለየት ሥራ ተከናውኗል፡፡

በጥናት ከተለየው የደረቅ ወደብ የግንባታ ቦታ ለሚነሱ 2ሺህ 544 ነዋሪዎችና የንግድ ድርጅቶች ተገቢውን የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ ሲካሄድ የቆየው ዝርዝር ጥናት ተጠናቋል፡፡

የጥናት ሰነዱ ለክልሉ ገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ለውሳኔ መላኩን የገለጹት ተወካዩ ለካሳ ክፍያው 190 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከ100 እስከ 500 ካሬ ሜትር ለመኖሪያና ለድርጅት የሚሆን የግንባታ ቦታ ለተነሺዎች በነፍስ ወከፍ ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም አቶ አድኖ ተናግረዋል፡፡

“በአሁን ወቅት ለተነሺዎች በተዘጋጀው ቦታ በ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ 3 ኪሎ ሜትር የመብራት መስመር ዝርጋታ የተከናወነ ሲሆን የትራንስፎርመር ተከላ ሥራም በቅርቡ ይጀመራል” ብለዋል፡፡

እንደ ተወካዩ ገለጻ የደረቅ ወደቡ መገንባት ሀገሪቱ በሱዳን በኩል ወደ ውጪ የምትልካቸውን የግብርና ምርቶችና የቁም እንስሳት ንግድ እንቅስቃሴ ያሳልጣል።

በተጨማሪም በሱዳን በኩል ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ማዳበሪያና ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብአቶችን በቀላሉ ከወደብ አጓጉዞ በማራገፍ የወደብ ኪራይ ወጪን ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል፡፡

ለአካባቢው ሕብረተሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ የከተማውን የንግድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት በኩል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መተማ ዮሐንስ ከተማ የሱዳን የድንበር ከተማ ከሆነው “ገላባት” ጋር ጥብቅ ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት ያለው ሲሆን የሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢ ሕዝቦችም ትስስር ዘመናት የዘለቀ መሆኑንም ተዘግቧል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.