የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከልና ለማጋለጥ የህግ አስከባሪ ተቋማት የጋራ እቅድ ይፋ ተደረገ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)-  በኢትዮጵያ በተለያዩ ደረጃዎች የሚፈጸም የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለማጋለጥና ክስ የመመስረት ተግባርን ተባብረው ለመስራትና መረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲቻል የሕግ አስከባሪ ተቋማት የጋራ እቅድ ይፋ ተደረገ።

ተቋማቱ የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሸን፣ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌደራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ናቸው።

ተቋማቱ በእቅዱ መሰረት በአዲሱ በጀት ዓመት ሙስናን በጋራ ለመከላከል በሚያስችላቸው እቅድ ላይ እየተወያዩ ነው።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሸን የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ፥ የጋራ እቅዱ ተቋማቱ በተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በተበታተነ መልኩ ሙስናን ለመከላከል ሲያካሔዱት የቆዩትን እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን ያግዛቸዋል ብለዋል።

ተቋማቱ ከዚህ በጀት ዓመት ጀምሮ የሙስና ወንጀልን የመመርመርና ክስ የመመስረት ተግባር በጋራ መስራትና መረጃዎችን መለዋወጥ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።

አሁን የሕግ ማስፈፀም ሥራው በአንድ ማዕከል በጠቅላይ አቃቤ ሕግና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲመራ መደረጉን ያስታወሱት አቶ አክሊሉ፤ ተቋማቱ በተናጥል የሚያገኙትን መረጃ በማደራጀትና ለሚመለከተው አካል በማቅረብ በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የፊደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሀብት ጥናትና ምርምር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ወርዶፋ በበኩላቸው፥ የጋራ እቅዱ ውጤታማና ቀልጣፋ የሆነ የሕግ ማስከበር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ይረዳል ብለዋል።

ለተቋማቱ በርካታ ተግባርና ኃላፊነትን በሰጠው በዚህ እቅድ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቅንጅታዊ እቅዱን ለመተግበር የሚያስችል አደረጃጀት መዘርጋት፣ በቂ የሰው ኃይልና ግብአት መመደብና ስምሪት የመስጠት ስራም እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

የታክስና ጉምሩክ፣ የሙስናና ሕገ ወጥ ንግድ ውድድር ወንጀሎች ላይ በፍርድ ቤት የሚደረግ ክርክር ደግሞ ለጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የተተወ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ የፍርድ ውሳኔዎች መፈፀማቸውን የመከታተልና የማስፈጸም፣ በምርመራ መዝገብ ላይ የተጠቀሱ ኤግዚቢቶች ላይ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ተግባርና ኃላፊነትም እንደተሰጠው ነው የገለጹት።

የታክስና ጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀልን በሚፈጽሙ ግብር ከፋዮችን ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሳምንት ቢያንስ አምስት ጊዜ የኦፕሬሽን ስራዎችን መስራት ደግሞ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መካከል እንደሚገኙበትም ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፥ በመዲናዋ በገቢና ግብር አሰባሰብ ስርአቱ ላይ የሚፈፀሙ የሕግ ጥሰቶችን፣ በንግድ ውድድርና ሸማቾች መብት ጥሰት ላይ የሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራትና የሙስና ወንጀልን በሕግ አግባብ አጣርቶ ለፍትሕ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስተዳደራዊ ምርመራ በሚያከናውንበት ወቅት ከፀረ ንግድ ውድድር ተግባር ውጪ ሊመረመሩ የሚገባቸው የሕግ ጥሰቶችን ለሚመለከተው አካል እንደሚያስተላልፍም ነው አቶ ተረፈ የተናገሩት።

የተጠናቀቁ የሙስና ወንጀል ምርመራ መዛግብት በሌላው አካል ከተፈለጉ ወይም የሚጠቅሙ ሆነው ሲገኙ ሰነዶቹን የማስተላለፍና የሙስና መከላከል ጥናቶችን ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው የመረጃ ልውውጥ ማድረግም በጋራ እቅዱ ውስጥ ተካቷል።

ድርጅቶቹ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው አዋጅ 943/ 2008 መደንጉ የሚታወቅ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.