የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ ሕገመንግስቱንና ሕገ መንገሰታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል አስቸኳይ ጊዜ ታውጇል።

መንግስት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅ፣ የአገርን ሰላምና ደህንንነት የማስከበርና የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት እውን በማድረግ የዜጎችን በነፃነት የመዘዋወር፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሀብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን እንዲሁም  የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚጥስና ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ  እየተስፋፋና እየተራዘመ  መሄዱን  መገንዘቡንም በመግለጫው አመልክቷል።

በተፈጠረው  ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ  ክፍሎች መንግስት የህግ ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግላቸው መንግስትን በተለያዩ መድረኮች መጠየቃቸውን አስታውሷል።

በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተጋረጠውን ይህን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመጠበቅ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አሰፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት አስታውቋል።

ስለሆነም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 ( ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አረጋግጧል።

አዋጁ በሚኒስትሮቸ ምክር ቤት ከታወጀበት ከየካቲት 09/2010 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.