የቡና የግብይት መጠንና ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል-የኢትዮጵያ ምርት ገበያ

(ኤፍ ቢ ሲ)- በ2010 ዓ.ም ጥቅምት ወር የተገበያየው ቡና የግብይት መጠንና ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገልጿል።

በወሩ የ2010 የቡና ግብይት ዋጋ በ58 በመቶ ማደጉን ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የጠቆመው።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥቅምት 2010 ዓ.ም በ22 የግብይት ቀናት 37 ሺህ 222 ቶን ምርት በማገበያየት የአጠቃላይ መርሃዊ የግብይት ምርት ዋጋውን 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ማድረሱን ጠቅሷል።

በወሩ 27 ሺህ 212 ቶን ቡና፣ 990 ቶን ቦለቄ፣ 8 ሺህ 990 ቶን ሰሊጥ እና 30 ቶን ማሾ መገበያየቱን ነው የገለፀው።

ቡና የአጠቃላይ ወርሃዊ ግብይቱን መጠን 73 በመቶ እንዲሁም የግብይቱን ዋጋ 87 በመቶ በመውሰድ በዚህ ወር ቀዳሚነቱን ይዟል።

በዚህ ወር የቡና ዋጋ በ8 በመቶ የጨመረ ሲሆን፥ ከመስከረም 2010ዓ.ም ግብይት ጋር ሲነፃፀር አጠቃላይ የግብይት ዋጋና መጠኑ እንደቅደምተከተላቸው በ58 በመቶ እና በ68 በመቶ አድጓል።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የተገበያየው ቡና የግብይት መጠንና ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ምርት ገበያው አስታውቋል።

ከቡና ግብይት ውስጥ ወደ ውጪ የሚላክ ቡና ግብይቱን በቀዳሚነት እየመራ ሲሆን፥ የግብይት መጠኑና ዋጋው በተመሳሳይ 72 በመቶ ድርሻ አለው።

ከዚህ በተጨማሪ 4 ሺህ 850 ቶን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ፥ 2 ሺህ 679 ቶን ለስፔሻሊቲ ቡና ግብይት ተፈፅሟል።

በቡና ግብይት በተለይ ስፔሻሊቲ ቡና በፈረሱላ ከፍተኛው 2 ሺህ 360 ብር ዝቅተኛው 940 ብር ተሽጧል።

የቦለቄ ግብይት በመጠን በ40 በመቶና በዋጋ 36 በመቶ የጨመረ ሲሆን፥ የሰሊጥ መሸጫ ዋጋ በ12 በመቶ አድጓል።

በወሩ 8 ሺህ 990 ቶን ሰሊጥ በ265 ሚሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ 68 በመቶ በግብይት መጠንና በ70 በመቶ የገበያ ዋጋውን በመያዝ ይመራል።

ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የሰሊጥ ግብይት መጠን በ29 በመቶ ዋጋው ደግሞ በ46 በመቶ ከፍ በሏል።

በወሩ 990 ቶን ነጭ ቦለቄ በ15 ሚሊየን ብር ሲገበያይ፥ ካለፈው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በግብይት መጠን የ40 በመቶ የግብይት ዋጋ የ36 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በጥቅምት ወር 30 ቶን ማሾ በ588 ሺህ ብር መገበያየቱን ምርት ገበያው አስታውቋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.