የባድመ ከተማ ነዋሪዎች የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ከህዝቡ ጋር ውይይት እንዲካሄድ ጠየቁ

(ኤፍ ቢ ሲ)- የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በኢትዮ – ኤርትራ ጉዳይ ይ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም የባድመ ከተማ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርስ ስምምነትንና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን የተቃወሙት ነዋሪዎች ዛሬ ረፋድ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ሰላም እንደሚፈልጉ ያነሱት ነዋሪዎቹ፥ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ህዝቡን ሳያወያይ ድንገት ውሳኔ ማሳለፉን አጥብቀን እንቃወማለን ብለዋል።

በዚህም ህይወት የተከፈለበትን መሬት አሳልፈን አንሰጥም ብለዋል ሰልፈኞቹ።

“እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንጅ ኤርትራ መሆን አንችልም” በማለትም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ነዋሪዎቹ በቀጣይ ከህዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ የመፍትሄ ሃሳብ መቅረብ እንዳለበትም ጠይቀዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳደር አቶ ፍጹም ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፥ የህዝቡን አቋም ወደሚመለከተው አካል እንድሚያደርሱ ገልጸዋል።

ከሚመለከተው አካል የሚሰጠውን ምላሽም ተመልሰው ከህዝቡ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉበት ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ዓርብ በኢሮብ ወረዳ በተመሳሳይ መልኩ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።

በሰልፉ ከዓገረሎኸማ፣ እንዳልጌዳ፣ ወርዓትለ፣ ዓሊተና፣ ሓራዘ ሰብዓታ፣ እንዳሞሳ፣ የደውሃን እና ዓራዕ ቀበሌዎች የተውጣጡ ሰልፈኞች ውሳኔውን ተቃውመውታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.