የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያለምንም አድልኦና ወገንተኝነት ህዝብና አገርን ለማገልገል መዘጋጀቱን አስታወቀ

(ኢዜአ)- የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያለምንም አድልኦና ወገንተኝነት ህዝብና አገርን ለማገልገል መዘጋጀቱን  ዋና ዳይሬክተሩ ጄኔራል አደም መሐመድ ገለጹ።

አገልግሎቱን እንዲመሩ በቅርቡ የተሾሙት አመራሮች ዛሬ በአዲስ አበባ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር ትውውቅ አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት ጄኔራል አደም እንደገለጹት “ተቋሙ መንግስትንና ህዝብ የሰጠውን ተልዕኮ ያለምንም አድልኦና ወገንተኝነት ለመፈጸም ዝግጁ ነው”።

ተቋሙ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት መስጠት በሚችልበት ደረጃ አስፈላጊው የማሻሻያ እርምጃ እንደሚወሰድ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተቋሙ የሚሰራ አካል ከፖለቲካ ፓርቲ አባል ነጻ ሆኖ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ህዝብና አገርን የሚያገለግል እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማንኛውም አደጋ ለመከላከል የተሰጠውን ግዳጅ በትጋት የሚሰራ መሆኑንም ጄኔራል አደም አመልክተዋል።

ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊቃጡ የሚችሉ ማንኛውም አደጋዎችን ቀድሞ የማወቅ፣ አደጋን የማስቀረት፣ አደጋ ከመድረሱ በፊትም የመንግስት አካላት አውቀው አፋጣን  እርምጃ እንዲወስዱ መረጃዎችን በመስጠት ህዝቡንና አገሪቷን ከአደጋ የመጠበቅ ስራም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመንግስት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ተቋሙ የድርሻውን በብቃት ለመወጣት ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከፖለቲካ አስተሳሰብና ከድርጅት አባልነት ነጻ ሆኖ በሙያ ላይ ብቻ ተመስርቶ ህዝብን ያለ አድልኦ ሊያገለግል የሚያስችል የማሻሻያ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ ።

ተቋሙ በህዝቡ ዘንድ በባለቤትነት መንፈስ እንዲታይ ለማስቻል የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት ጄኔራል አደም እንደ ፖሊስ፣ መከላከያ ሰራዊትና ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.