የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም ከኃላፊነታቸው ተነሱ

(ሪፖርተር)- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣንን ከአራት ዓመታት በላይ በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ዘርዓይ አስገዶም ከኃላፊነታቸው ተነሱ፡፡

አቶ ዘርዓይ በምን ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ባይታወቅም፣ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተሹመው የነበሩት አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፊርማ ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ወጪ በተደረገ የሹመት ደብዳቤ፣ አቶ ሰለሞን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ ተሹመዋል፡፡

አቶ ሰለሞን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) አባል ሲሆኑ፣ ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እስከ ግንቦት 2 ቀን 2010 ድረስ ቆይተዋል፡፡

የሕወሓት አባል የሆኑት አቶ ዘርዓይ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለበርካታ ዓመታት መሥራታቸው ይታወሳል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.