የታሸጉ ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዘዙ

(ሪፖርተር)- በሚያደርሱት የአካባቢ ብክለት ምክንያት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታሸጉት ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች፣ ከረቡዕ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍተው መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማዘዛቸው ተሰማ፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካይት በተወሰደው ዕርምጃ መሠረት፣ ኤሊኮ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካን ጨምሮ፣ ባቱ ቆዳ ፋብሪካ፣ ድሬ፣ አዲስ አበባ፣ ዋልያ፣ እንዲሁም ጫማ የሚያመርተው የቻይናው ሉዊንግ የተባሉት ቆዳ ፋብሪካዎች ታሽገው ሰንብተዋል፡፡ አስተዳደሩ ዕርምጃውን ከመውሰዱ በፊት ለዓመታት የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓታቸውን እንዲያስተካክሉ ሲጠይቅና ሲያስጠነቅቅ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ የቆዳ ፋብሪካዎች የፍሳሽ አወጋገዳቸውን አጣርተው የሚለቁበት ሥርዓት እንዲገነቡ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እየተራዘመ፣ ከአምስት ዓመታት በላይ መቆየታቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ይሁንና ጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወሰደ ድንገተኛ ዕርምጃ ስድስቱ ቆዳ ፋብሪካዎች ያለማስጠንቀቂያ እንዲታሸጉና ሥራ እንዲያቆሙ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ሰፊ የዕፎይታ ጊዜ እንደተሰጣቸው ባይክዱም፣ በድንገት ያውም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ታሽገው እንዲቆዩ በመደረጋቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ጉዳት ለመንግሥት ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ለመንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ የፋብሪካዎቹ መዘጋት 3,000 ሠራተኞቻቸውን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ከማስገደዱም በላይ፣ ያለ ሥራ ለተቀመጡበት ጊዜ በወር ከ7.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማድረግ እንደሚገደዱ ማስታወቃቸው ተሰምቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፋብሪካዎቹ በመዘጋታቸው ሳቢያ በምርት ሒደት ላይ የነበሩ 28.7 ሚሊዮን የሚያወጡ ጥሬ ቆዳና ሌጦን ጨምሮ፣ ያለቀላቸው የቆዳና ሌጦ ምርቶች ለብልሽት መጋለጣቸው እንደሚያሠጋው ማኅበሩ ማስታወቁን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

ስድስቱ የቆዳ ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት 6,000 የበግና የፍየል ሌጦ፣ እንዲሁም 800 የከብት ቆዳ በአማካይ እያመረቱ የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ ዕርምጃው እንዲጤን የጠየቀው ማኅበሩ፣ የአካባቢ ብክለት እንደሚያሳስበው አስታውቆ በስድስት ወራት ውስጥ ሁሉም ፋብሪካዎች የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ሥርዓታቸውን እንደሚገነቡ፣ ለዚህም ግዴታ መግባታቸውን ለመንግሥት እንዳስታወቀ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጊዜ ውስጥ ተገቢውን ደረጃ የጠበቀ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ባልገነቡት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ ማኅበሩ እንደሚደግፍ በመግለጽ፣ ለአሁኑ የተዘጉት ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

ይህ ጥያቄ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል የቀረበላቸው አቶ ኃይለ ማርያም፣ ማኅበሩ ፋብሪካዎቹን በመወከል በገቡት ግዴታ መሠረት እንደሚያከናውኑ መተማመኛ በመስጠቱ የተዘጉት ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ማዘዛቸው ታውቋል፡፡ ማኅበሩ እያንዳንዱን ሒደት ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲዋቀርና ሥራውን እንዲከታተል ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከ20 ጊዜ በላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፎ ምላሽ ማጣቱን በመግለጽ በፋብሪካዎቹ አድራጎት ተስፋ መቁረጡን ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የቆዳ ፋብሪካዎቹ የሚለቁት ፍሳሽ ቆሻሻ ከአካባቢ ብክለት ባሻገር በነዋሪዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱ፣ በተለይም በሕፃናት ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በማስመልከት ነዋሪዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.