የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ እግረኞችን መቅጣት የሚያስችለው መመሪያ ወደ ስራ ሊገባ ነው

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የመንገድ ትራፊክ ደንብን ተላልፈው የሚገኙ እግረኞችን መቅጣት የሚያስችለው መመሪያ ወደ ስራ ሊገባ ነው።

መመሪያው በሚቀጥለው አመት መጀመሪያ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ነው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ያስታወቀው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም እንደተናገሩት፥ መመሪያውን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችለው ዝግጅት እያጠናቀቀ ነው።

መመሪያው ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ መንገድ ያቋረጠን ጨምሮ በብረትም ሆነ በግንብ ተለይተው የታጠሩ መንገዶችን ዘሎ ያቋረጠ እግረኛን ከ40 እስከ 80 ብር እንዲቀጣ አስቀምጧል።

በማንኛውም ሁኔታ የመንገድ ላይ ንግድ በሚፈፅሙ፣ ቁሳቁሶችን መንገድ ላይ በሚያስቀምጡና በአጠቃላይ ለእግረኞች እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ አካላት ላይም መመሪያው ቅጣት ይጥላል።

ለተሽከርካሪ በተፈቀደ መንገድ ላይ ያለበቂ ምክንያት የሚያቆም ወይንም የሚነዳ አሽከርካሪም ከቅጣት አያመልጥም።

መመሪያው ተፈፃሚ ሲሆን የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት መክፈል የማይችሉ እግረኞች ተመጣጣኝ ማህበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል።

ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2008 ዓ.ም ብቻ ከ4 ሺህ 350 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከእነዚህ ውስጥም 43 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች ናቸው።

ለጉዳቱ የአሽከርካሪዎች ችግር ከፍተኛውን ድርሻ ቢይዝም የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም፣ የስነ ምግባር እና ህግን ያለማክበር ችግሮችም የጎላ ሚና ይጫወታሉ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ እንደሚናገሩት፥ እግረኞች በቸልተኝነት የሚፈጽሙት የመንገድ አጠቃቀም ችግር ለበርካታ የትራፊክ አደጋዎች መከሰት ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል።

በእግረኞች ጥፋት ሳቢያ የሚከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ገልፀዋል።

ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ በእግረኛው የመንገድ አጠቃቀም ችግር የሚከሰተው ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል።

አብዛኛው የመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚከሰተው በምሸት ሳይሆን በቀን፤ የመንገድ መሰረተ-ልማቱ ባልተሟላበት ሳይሆን በተሟላበት መሆኑ አስገዳጅ መመሪያዎች ወደ ትግበራ እንዲገቡ ማድርጉን ነው የትራንስፖርት ባለስልጣን የገለፀው።

በሀገሪቱ ደንብ የሚተላለፉ እግረኞችን ለመቅጣት ከ1956 ጀምሮ ህግ የወጣ ቢሆንም እስከዛሬ ወደ ትግበራ አልተገባም።

እግረኞችን ለመቅጣት የሚያስችለው ደንብ ቁጥር 395/2009 የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ በታህሳስ ወር ፀድቋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገርናቸው የመዲናዋ አሽከርካሪዎችና ነዋሪዎች መመሪያው ተግባራዊ መሆኑ በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ የሚፈጠሩትን ተፅዕኖዎች ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።

ባለስልጣኑ መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረጉ አስቀድሞ የጠፉና የደበዘዙ የእግረኛ መተላለፊያ መስመሮችን እና የመንገድ ዳር ምልክቶችን የማስተካከል ስራ እንደሚሰራ አስታውቋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.