የቻይና፣ የደቡብ ኮሪያና የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከትመዋል

(ኢዜአ)- አለም አቀፍ አልባሳት አምራቾች በፍጥነት በማደግ ላይ ወዳለችው ኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን ለማፍሰስ እየተሳቡ ነው ፡፡

ኒኪ ኤሽያን ሪቪው  የተባለው ድረገጽ እንደዘገበው በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በተቀመጠችውና በፍጥነት በማደግ ላይ ባለችው ኢትዮጵያ ከቻይና ፣ህንድና ደቡብ ኮሪያ የመጡ አልባሳት አምራቾች ፋብሪካቸውን ከፍተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የአልባሳት አምራቾች ፍላጎት መሰረት የሆነው የኢትዮ – ጅቡቲ የባቡር መስመር እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የባቡር መስመሩ በአገሪቱ ካሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀላሉ ምርቶችን ለማጓጓዝ ያስችላል፡፡

እኤአ በ 2015 በተከፈተውና  በ150 ሔክታር መሬት ላይ ባረፈው የቦሌ ለሚ ፓርክ ከቻይና፣ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ የመጡ ትላልቅ ኩባንያዎች የጨርቃ ጨርቅ፣የአልባሳትና የቆዳ ጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ከፍተው እየሰሩ ነው ብሏል ዘገባው፡፡

በደቡብ ኮሪያው ሺን ቴክስታይል ሶሊሽን የሚተዳደረው ፋብሪካ የስፖርት ትጥቆችን ያመርታል፡፡ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ እንደተናገሩት ከምርታቸው 60 በመቶ ወደ አውሮፓ ፣ 20 በመቶ ወደ አሜሪካ እና የተቀረውን ወደ እስያ ይልካሉ፡፡

በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የጃፓኑ የልብስ ማምረቻና መሸጫ  ዩኒኪሎ አልባሳት የመውሰድ ፍላጎት ማሳየቱን ማናጀሩ ጠቅሰዋል፡፡

ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ግስጋሴ

የኢትዮጵያ የወጪ ምርት በአብዛኛው ቡና፣ወርቅና የቆዳ ውጤቶች ቢሆኑም መንግስት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን እያስፋፋ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪና የኢንዱስትሪ ልማት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ እቁባይ ኢትዮጵያን ከአዝጋሚው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማውጣት ወደ ኢንዱስትሪ መዳረሻነት ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ድረ ገጹ ጠቅሷል፡፡

አገሪቱን እኤአ በ 2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ለተያዘው ግብ መሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ አጋዥ ነው፡፡በቅርቡ የተመረቀው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርከ ከያዛቸው 15 ኩባንያዎች መካከል የአሜሪካው ልብስ አምራች ፒ ቪ ኤች አንዱ ነው፡፡

በኩባንያው የሚሰሩት 280 ባለሙያዎች ለተለያዩ አለም አቀፍ የልብስ አምራቾች ምርታቸውን የሚያዘጋጁላቸው ሲሆን ከነዚህ መካከል የሚጠቀሰው ካልቪን ክሌን ለአሜሪካና አውሮፓ ገበያ የሚውሉ አልባሳትን ከፋብሪካው ይረከባል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ዝቅተኛ የጉልበት ክፍያ ለአልባሳት አምራቾች መሰባሰብ ምክንያት መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል፡፡በኢትዮጵያ ያለው ወርሃዊ አማካይ ክፍያ 50 ዶላር ሲሆን በኬንያ 140-160 ዶላር፣በባንግላዴሽ ከ 70-90 ዶላር ፣በቬትናም ከ 150-170 ዶላር እንዲሁም በቻይና 400-500 ዶላር የጉልበት ዋጋ ይከፈላል፡፡

የአገሪቱ የህዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠና ወጣት ሰራቶችን በብዛት የያዘ ነው፡፡ይህ እምቅ ሐብት ደግሞ ለአልባሳት አምራቾች መበራከት ምክንያት ሆኗል፡፡አገሪቱ በስፋት እያከናወች ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታና ማስፋፊያ ሌላው መስህብ ተደርጎ ተወስዷል፡፡አገሪቱ የባህር በር ባይኖራትም የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ችግሯን እንደሚፈታላት ተገልጿል፡፡

መንግስት ሞጆ ላይ የመሰረተው የደረቅ ወደብ አገልግሎት ከባቡር መስመሩ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ከኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች  የሚነሱ ምርቶች ከዚሁ ጣቢያ በቀጥታ ወደ ጅቡቲ የባህር በር ይላካሉ፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ ከአዲስ አበባ የሚነሱ ምርቶች ጅቡቲ ለመድረስ ሶስት ቀን ይፈጅባቸው ነበር፡፡አዲሱ የባቡር መስመር ግን ምርቶችን በዘጠኝ ሰአት ውስጥ ጅቡቲ ወደብ ለማድረስ ያስችላል፡፡

ተጨማሪ ንግድን መሳብ

በአሁኑ ወቅት ወደ አገሪቱ በስፋት እየገቡ ያሉት የአልባሳት አምራቾችና ቀላል ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ነገር ግን ጄኔራል ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ የህክምና መሳሪያዎችን ለማምረት እቅድ የያዘ ሲሆን ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ በበኩሉ ከአገር ውስጥ ባለሐብት ጋር በሽርክና ፕሪንተር ለማምረት እየሰራ ነው፡፡

በተጨማሪ ሀዩንዳይ ሞተር ባለፈው ግንቦት ወር ከአገር ውስጥ ባለሐብት ጋር ስምምነት በማሰር የንግድ መኪናዎችን ለመገጣጠም የሚያስችለውን ፋብሪካ ለመገንባት ተዘጋጅቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሆነ በአፍሪካ  በኢንቨስትመንት ፈሰስ ቀዳሚ የሆነችው ቻይና ለአገሪቱ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ዋነኛ አጋር መሆኗን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.