የንፋስ ሀይል ማመንጫን በግሉ ዘርፍ ለማልማት መታቀዱ ተገለፀ

(EBC)- በንፋስ ኃይል ልማት ዘርፍ በGTP II ከተያዙት ፕሮጅከቶች በአብዛኛው በግሉ ዘርፍ እንዲከናወኑ መታቀዱን የውሃ፤ መስኖና ኤሌክትሪሲቲ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ጥናትና ክትትል ዳይሪክተር አቶ ሳህሌ ታምሩ እስካሁን የግሉ ዘረፍ ተሳትፎ እንዳልነበረ አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ሳህሌ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ከዴንማርክ መንግስት በተገኘ ድጋፍ መሰረታዊ የአሰራር ሰነዶች፣ የጨረታ፣ የኃይል ሽያጭ ስምምነት፣ የዋስትና የህግ ማእቀፎችን ማዘጋጀት እንዲሁም በግሉ ዘርፍ በቅድሚያ የሚለሙ ፕሮጅክቶችን የመለየት ስራ በመከናወን ላይ ነው፡፡

በአለም ባንክና በዴንማርክ መንግስት ድጋፍ ከዚህ በፊት የአገሪቱን ንፋስ ኃይል አቅም በተመለከተ የተሰሩ ጥናቶችን የሚያጠናክር ዝርዝር የንፋስ ኃይል አቅም ጥናት በመካሄድ ላይ ሲሆን እ.ኤ.አ 2019 ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በGTP II እንዲለሙ ከተያዙት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል አይሻ I (300 ሜ.ዋ)፣ አይሻ II (120 ሜ.ዋ)፣ አዳማ III (150 ሜ.ዋ)፣ ደብረ ብርሃን (100 ሜ.ዋ) የሚገኙ ሲሆን በተጨማሪም 1200 ሜ.ዋ ከተለያዩ የንፋስ ኃይል ፕሮጅከቶች ለማመንጨት ታቅዷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከንፋስ ሃይል በአጠቃለይ 324 ሜ.ዋ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም የተፈጠረ ሲሆን ይህም ከአዳማ I (51 ሜ.ዋ)፣ ከአዳማ II (153 ሜ.ዋ) እና ከአሸጎዳ (120 ሜ.ዋ) የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች የተገኘ ነው፡፡

የንፋስ ኃይል ማመንጫዎቹ በጥሩ ሁኔታ ኃይል እያመነጩ እንደሆነም አቶ ሳህሌ በውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ የነበረውን ከፍተኛ ጫና በመቀነስ በኩል አውንታዊ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.