የአሸንዳ በዓል ከባህላዊ እሴቱ ባለፈ የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለን ነው — የመቀሌ ከተማ ነጋዴዎችና ልብስ ሰፊዎች

(ኢዜአ)- በትግራይ ክልል በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የአሸንዳ በዓል ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎችና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ገለጹ።

የአሸንዳ በዓል  በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ ፣ የባህልና የትምህርት ኮሚሽን (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ባህላዊ  ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

በመቀሌ ከተማ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ሥራ የተሰመሩ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዓሉ ለሥራቸው ማንቀሳቀሻ የሚሆን ገቢ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል።

በከተማው የ”ሕዳሴ ልብስ ስፌት” ባለቤት ወጣት ገብረሕይወት ግርማይ እንዳለው ልጃገረዶች የአሸንዳ በዓልን ለማክበር በየዓመቱ ለባህላዊ ልብሶች ፣ በአንገት ለሚንጠለጠሉ የማስጌጫ ቁሶችና ለፀጉር ሥራ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣሉ፡፡

በዓሉ ሲደርስ በልብስ ስፌት የሚተዳደሩ ባለሙያዎች ያለእረፍት ለ24 ሰዓት በሥራ የሚጠመዱበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሷል።

እርሱም በበዓሉ ሰሞን ገበያው ስለሚደራ ከ30 እስከ 40 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኝ ተናግሯል።

“የአሸንዳ በዓል ሲቃረብ የልብስ ስፌት ሥራ አቋርጠው የነበሩ ባለሙያዎች ሳይቀር ተመልሰው ወደ ሥራው ይገባሉ” ያለው ደግሞ ወጣት ተስፋይ ኃይሉ ነው፡፡

ዘንድሮ ለበዓሉ የሚሆን ባህላዊ ልብሶችን በመስፋት እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ወጣት ተስፋይ ተናግሯል፡፡

ለአሸንዳ በዓል ባህላዊ ልብስ መግዣን ጨምሮ ለጌጣጌጥና ለፀጉር ሥራ እስከ 2 ሺህ ብር ወጪ እንደምታደርግ የገለፀችው ደግሞ ለበዓሉ የሚሆናትን ባህላዊ ልብስ በመግዛት ላይ የነበረችው ወጣት መአዛ አሸብር ናት፡፡

ሌላው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ወልዳይ ዘርአይበኩሉ” የዘንድሮ የአሸንዳ በዓል ለየት የሚያደርገው በበዓሉ የሚሳተፉ ሴቶች ባህላዊ የሃገር ውስጥ ልብስ ብቻ እንዲለብሱ መወሰኑ  ነው”  ብሏል።

“ሴቶች በባህላዊ የሀገር ልብስ ደምቀው በዓሉን እንዲያከብሩ መደረጉ እንደ አገር ተጠቃሚ ያደርገናል” ሲል ወጣት ወልዳይ ተናግሯል።

የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ሕሉፍ እንደገለፁት የአሸንዳ በዓልን በዓለም ቅርስነት  ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ።

ዘንድሮም ይህንኑ ጥረት የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የዘንድሮ የአሸንዳ በዓል በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከነሐሴ 15 እስከ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በድምቀት ይከበራል ።

በዓሉ “አገር በቀል ባህላዊ እሴቶቻችንና ቅርሶቻችንን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከፍ እናድርግ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

በበዓሉ ላይ የተለያዩ የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.