የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መዲናዋን አሸለማት

(ኢዜአ)- አዲስ አበባ የአየር ንብረት ተጽዕኖን የሚቀንስ ቀላል ባቡር በመጠቀሟ የዓለም አቀፍ የእውቅና ሽልማት ባለቤት ሆነች።

ከተማዋ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ላይ በሚሰራው “ሲ 40’’ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም ተሸላሚ የሆችው ከዓለም ታላላቅ ከተሞች ጋር ተወዳድራ ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ ነው።

ተቋሙ ባቡርን በስፋት የሚጠቀሙ የዓለም ከተሞችን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በመቀነስ ረገድ ባለፈው ጥቅምት ወር በሜክሲኮ የተለያዩ አገራት ከተሞችን በማወዳደር ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆኗን አስታውቋል።

የተቋሙ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስተር ሃስቲንግስ ቺኮኮ ትናንት ሽልማቱን ለመዲናዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ሲያስረክቡ እንደገለጹት ከተማይቱ የእውቅና ያገኘችው ተቋሙ ካወዳደራቸው ከ100 በላይ ከተሞች አንደኛ በመውጣቷ ነው።

“ሽልማቱ የጠንካራ አመራር ውጤት ምልክት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ “አዲስ አበባ ያደጉ ከተሞች ያልቻሉትን በማድረግ ለሽልማት መብቃቷ ልዩ ያደርጋታል” ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካዎቹ ኬፕታውንና ጆሀንስበርግ እንዲሁም የጋናዋ አክራ በአፍሪካ በውድድሩ ከተሳተፉ ከተሞች መካከል ይጠቀሳሉ።

ለመጨረሻ ዙር ከደረሱት አምስት ተወዳዳሪ ከተሞች መካከል የቻይናዋ ሁዋን፣ የአሜሪካዋ ሂውስተን፣ የታይዋኗ ኒውኢነርጂ ከተሞች ይገኙበታል።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ ”ሽልማቱ የፖሊሲና የጠንካራ አመራር ውጤት ነው፤ ይህንን ዓለም አቀፍ  ሽልማት ማሸነፋችን በሌሎች የከተማ መወዳደሪያ መስፈርቶችም አሸናፊ ለመሆን ጠንክሮ ለመስራት ትልቅ ግብዓት ይሆነናል” ብለዋል።

ሽልማቱ ለአዲስ አበባ እንደ አምባሳደር በመሆን በዓለም ታላላቅ ከተሞች ላይ ዕውቅና እንዲኖራት ያደርጋታል ሲሉም ከንቲባ ድሪባ አክለዋል።

“ሲ 40” ዓለም አቀፍ ተቋም ከተሞች ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ በሰሩት ጥሩ ስራ በየሁለት ዓመቱ ጉባዔ እያካሄደ ሽልማት የሚሰጥ ተቋም ነው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2005 በእንግሊዝ የተመሰረተው “ሲ 40’’ አዲስ አበባን ጨምሮ ከ650 ሚሊዮን በላይ ህዝቦችን የሚወክሉ 90 የዓለም ታላላቅ ከተሞችን በአባልነት አቅፏል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.