የኢህአዴግ ውሳኔ ፋይዳና ስጋት

(አዲስ ዘመን)- የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስትያ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በደም ለተሳሰሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ እንደሚተገብር ወስኗል፡፡ ይህ ውሳኔ ለሁለቱ ሃገሮች ሰላማዊ ግንኙነት ፋይዳው የጎላ ቢሆንም ስጋቶችም ይነሳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በሰጡት ማብራሪያ፤ የሁለቱ አገሮች ለሃያ ዓመታት የቆዩበትን ሁኔታ ‹‹ሰላምም የሌለበት ጦርነትም የሌለበት›› ሳይሆን ‹‹ሞት አልባ ጦርነት›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ምክንያቱም ላለፉት ሃያ ዓመታት በድንበር አካባቢ ሞት ባይኖርም ለጦርነት የሚያስፈልግ ወጪ፣ ዝግጅት፣ ስልጠና እና ውጥረት ነበር፡፡ በመሆኑም ይሄ ሁኔታ ቆሞ በተሟላ አቅም ወደ ሰላም መሻገር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት ወራት በኢትዮጵያ የመጣው የሰላም ድባብም ለቀጣናው ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ዕርምጃም ከአህጉራዊ ኃላፊነት የሚመነጭ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ምሑሩ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ መቀበሏ ‹‹እሰየው›› የሚያስብል ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የሁለቱ አገሮች ጉርብትና እንደ ብዙዎች አገሮች ጉርብትና በቀላሉ የሚታይ አይደለም›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከሁለት ሺ በላይ ዓመት በአንድነት የቆዩ ተመሳሳይ ሕዝቦች ቢሆኑም ባለፉት 20 ዓመታት የገቡባቸው ውስብስብ ችግሮች ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ በመሆኑም የዘላቂ ሰላም ጥቅምና ፋይዳ ከሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በላይ ሊገነዘበው የሚችል ሕዝብ ባለመኖሩ መንግሥታቱ ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ቀጣይ ሂደት መሻገር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ስምምነቱ ለሁለቱም አገሮች ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሩ፤ ከኢኮኖሚ አንፃር ኢትዮጵያ የዓመታት የአማራጭ ወደብ ጥያቄ ምላሽ ያገኛል፣ ለኤርትራም ወደቡን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ትችላለች፡፡ ኤርትራ በኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ከበለፀገች ትልቁ ገበያዋ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ በጥራጥሬና አብዛኞቹን የተፈጥሮ ሀብት ውጤቶች በስፋት ለኤርትራ ማቅረብ የሚያስችል ዕድል ይፈጠርላታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥቅም ደግሞ እርቅና ሰላም ማስፈኑ ወሳኝ ነው፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ፤ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት በተመለከተ ቀድሞም ቢሆን ልዩነት የነበራት በውሳኔው ላይ ሳይሆን በአተገባበሩ መሆኑን በማስታወስ አሁንም የተለየ አዲስ ነገር አለመፈጠሩን ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም አሁንም ኢትዮጵያ እንደተለመደው በአካባቢው ላይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያሳየችው ተጨማሪ ተነሳሽነት ነው ይላሉ፡፡
‹‹ወሳኙ ጉዳይ ግን ለምን ውሳኔው አሁን ሆነ? የሚለው ነው›› የሚሉት ፕሮፌሰር መረሳ፣የቀድሞው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ዶናልድ ያማማቶ ከወራት በፊት ሁለቱም አገሮች በመሄድ በድንበር ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ውሳኔው በሌሎች አገሮች ጫና ስላለመተግበሩ ማረጋገጡ ላይ ነው፡፡
በሌላ በኩል የሩሲያና የአሜሪካ መሪዎችም በተቀራራቢ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ሌሎች የዲፕሎማሲ ግፊቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያብራራሉ፡፡ ቻይናም የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ይዛ ወደቀጣናው ብቅ ማለት ከጀመረች ቆይታለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ነባራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ቢኖሩም ከምንም በላይ የሚቀድመው ከውሳኔው ባሻገር የሁለቱ አገሮችን ሕዝቦችና የአወዛጋቢዋን ባድመ አካባቢ ሕዝቦች ፍላጎት ማጤን ይገባል ይላሉ፡፡
የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሑሩ ፕሮፌሰር ገብሩ፤ ውሳኔውን በተመለከተ ከሌሎች አገሮች ግፊት ይልቅ አገራዊ ውጤቱ ላይ ማተኮር ይገባል ይላሉ፡፡ ፋይዳው ከሁለቱ አገሮች ቀጥተኛ ጥቅም ባሻገር በቀጣናው ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ የአሜሪካም ሆነ የሩሲያ እንዲሁም የቻይና ፍላጎት ምንም ይሁን ምን ወደጋራ ጥቅም ማዞር የሚቻለው በቅድሚያ ሁለቱ አገሮች ሰላም ሲፈጥሩ ነው፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የገልፍ አገሮችን ሽኩቻ በጥንቃቄ መፈተሽ የሚቻለውም በሁለቱ አገሮች ሰላማዊ ግንኙነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም መፍጠር ከቻሉ መሰል ሽኩቻዎችን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻሉም መቀነስ አይከብዳቸውም፡፡
ኢትዮጵያ ለዓመታት የሰላም እጇን ስትዘረጋ ቆይታለች፡፡ የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ሰበቦችን በመደርደር የሰላም ጥሪውን ሲገፋ ኖሯል፡፡ ‹‹የኤርትራን መንግሥት መተንበይ ያስቸግራል›› የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሩ፤ በቀጣይም ይሄ ሁኔታ የስምምነቱ ተፈፃሚነት በጥርጣሬ ለመመልከት ያስገድዳል፡፡ ይሄን ስጋት ለመቀነስም የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ተቀራርበው በቀጣይ ሂደቶች ዙሪያ ተሳታፊ መሆን ይገባቸዋል፡፡
ስጋቱን የሚጋሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር መረሳ፤ ስምምነቱ ለኤርትራ ሕዝብ ሳይሆን ለኤርትራ መንግሥት መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ነገር ግን ስጋቱ ቢኖርም የኤርትራ መንግሥት አሁን ካለበት የዲፕሎማሲ ጫና አንፃር ቀጣይ ድርድሮችን ይገፋል የሚል ግምት አይኖርም፡፡ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበትም የኢትዮጵያ አቋም መነሻ በግፊት ሳይሆን ለሁለቱ ሕዝቦች ሰላም እና ጥቅም ሲባል የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይገባታል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፖለቲካ መንፈስ የጀመረው የለውጥ ነፋስ በኤርትራም እንዲደገም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ፕሮፌሰር ገብሩ እንደሚገልጹት፤ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ተፅዕኖ ለዘመናት የቆየው የአካባቢው የፖለቲካ ችግር በሂደት ለሁለቱ አገሮች አለመግባባት ምንጭ ሲሆን ቆይቷል፡፡ ከኤርትራ ነፃነት በኋላም አገሮቹ ሰላም የነበሩ ቢሆንም ከተለያዩ የኢኮኖሚ የበላይነት ፍላጎቶች ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግሥት የባድመን ጉዳይ ያለመግባባት ምክንያት አድርጎ ቆይቷል፡፡ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ዜጎች ሕይወት አልፎ በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአሜሪካ መንግሥት እና በአውሮፓ ሕብረት ተሳትፎ የአልጀርስ ስምምነት መካሄዱን ይገልጻሉ፡፡
በወርሃ ታሕሳስ 1993 ዓ.ም በአልጄሪያ መዲና የተፈፀመ ስምምነት ሁለት ጉዳዮችን በዋናነት ያካተተ ሲሆን፤ የድንበር ማካለል ስምምነትና በጦርነቱ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት የሚፈፀም ካሳ ያካተተ ነው፡፡ በስምምነቱ መሰረት በሁለቱ አገሮች መካከል የመሬት ልውውጥ የሚደረግ በመሆኑ ኢትዮጵያ በአተገባበሩ ዙሪያ ውይይት ማድረግን አስቀድማ ቆይታለች፡፡ የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ የስምምነት ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲተገበር የሚል አቋም ይዞ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሁለቱ አገሮች ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያለሰላም ያለጦርነት እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ያልተጠበቀና ከጥሪ በላይ የተራመደ ውሳኔ በማስተላለፍ ለዘላቂ ሰላም ያላትን ፅኑ ፍላጎት አሳይታለች፡፡ ይሄም ለኤርትራ መንግሥት የእስከአሁኑ ‹‹ምክንያት›› በቂ መልስ የሰጠ ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን ዕርምጃ ያለምንም ሁኔታ ተቀብሎ ካልተገበረ ለሁለቱም አገሮች ፖለቲካዊ ውድቀት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ በቀጣናው የተጀመረውን ሽኩቻ አሳድጎት ደካማ መንግሥታትን የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.