የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች የማቀራረብቡ ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

(ኢዜአ)- የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን ለማቀራረብ የተጀመረው ጥረት ስኬት እንዲያመጣ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ሰለብርቲ ኢቨንትስ ”የሠላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ይበልጥ ለማቀራረብ ያለመ የውይይት መድረክ  ትላንት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ “የአገሮቹ ሕዝቦች ቀድሞ የነበራቸውን ወንድማማችነት እንዴት መመለስ ይቻላል?” በሚለው ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።

የህዝቦቹን አንድነት ለመመለስ እንዴት ዓይነት መንገድ መከተል አለብን? ዓላማውና መደረግ በሚገባው እንቅስቃሴ ዙሪያ በአሜሪካ ጊንግስ ኮሌጅ መምህር ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጹሁፍ አቅርበዋል።

ፕሮፌሰር መድሃኔ ባቀረቡት ጹሁፍ እንዳሉት፤ ሠላም ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ህዝቦቹ እንዲረዱት አጀንዳ ቀርጾ መንቀሳቀስ ይገባል።

በተለይ ምሁራን አለመግባባት በሚታይባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማት እንዲፈጠር የሚሰሩትን ሥራ ማጉላት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በመራራቃቸው ያጡትን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ ትኩረት አድርጎ ማስገንዘብ እንደሚገባ ነው ፕሮፌሰሩ ያነሱት።

የሁለቱ አገር ሕዝቦች ብሄራዊ ደህንነት ፍላጎት የት ጋ  እንዳለ ግልጽ ማድረግና የጋራ መግባባት እንዲፈጠር መስራት እንደሚያስፈልግም እንዲሁ።

የውይይቱ ተሳታፊ መምህር ገብረኪዳን ደስታ በበኩላቸው፤”የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች አንድ ነበሩ በጉንደትና ጉራ፣ ከኩፊት እስከ መተማ ጦርነቶች ድረስ በጋራ በመሆን ታሪክ ጽፈዋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኢዴፓ/  አባል አቶ ልደቱ አያሌው በሰጡት አስተያየት ”አሁን ያለው ትውልድ የችግሩ ፈጣሪ ባይሆንም ግን የችግሩ ተጎጂ ነው” ብለዋል።

የሁለቱን አገር ሕዝቦች ለማቀራረብ የተጀመረው ጥረት ትልቅ ዓላማን ያነገበ መሆኑን የገለጹት አቶ ልደቱ፤  በተለይ ወጣቶች ይሄን ጉዳይ አንግበው መስራታቸው እንደሚበረታታ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የኤርትራ ስደተኞች ተወካይ ግርማይ ባይራዱ በበኩሉ፤ ”በኢትዮጵያ መብታችን ተጠብቆ እየተንቀሳቀስን ነው፤ ከልማቱና ከሠላሙ  ተቋዳሽ ሆነናል ከዚህ በላይ ፍቅር የለም” ሲል ነው የገለጸው።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ “ጥላቻ አልነበረንም ጥላቻ ከነበረም ከቀድሞ ሥርዓት ጋር ነው። አሁን ግን ያለውን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመን የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ሠላም ለማጎልበት መስራት ይኖርብናል” ብሏል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ ኮሚቴ ከሁለቱም ወገን ያካተተ እንደሚቋቋም ታውቋል።

700 ኢትዮጵያዊያና ኤርትራዊያን የሚሳተፉበት የፓናል ውይይት ይደረጋል፤ የሁለቱ አገሮች አርቲስቶችም የሚሳተፉበት ኮንሰርት ለማዘጋጀት መታቀዱም ተገልጿል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.