የኢትዮጵያ ህዳሴ ስንል …

ካነበብኩት

(ሸጊት ከድሬ) “የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ጉዞም ነው፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያ ህዳሴ ስንል ህዝቦቻችን ከሺ ዓመታት በፊት ደርሰውበት የነበረውን የስልጣኔ ደረጃ ማድነቃችን፣ በዚሁ ውጤት መኩራታችንና አሁንም ተመልሰን ከሰለጠኑት አገሮች ጋር ለመሰለፍ መመኘታችንና ቆርጠን መነሳታችንን መግለፃችን ነው፡፡ ገናናውን የህዝቦቻችንን ታሪክ ለመድገም መከጀላችንን የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ገናና ታሪካችን ሂደት ብዝሃነታችንን ማስተናገድ ተስኖን፣ ልማቱን የሚያፈጥን አመራር መፍጠር አቅቶን ከተስፈኞችና ለማኞች ጎራ የተሰለፍንበትን የውርደት ታሪካችንን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግደን አዲስ ገናና ታሪክ ለመፃፍ ቆርጠን መነሳታችንን ማመላከታችንም ነው፡፡

ባለፈው ታሪክም ላይ የወደፊት ጉዞውን ማመላከታችን ነው፡፡ የውርደታችን ምንጭ የነበሩትን ነገሮች በማስወገድ የኢትዮጵያን ህዳሴ በአዲስ መሰረት ላይ ለመገንባት አገራችንን ስር ነቀል በሆነ አኳኋን ለማደስ መነሳታችንን የሚያሳይ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ሲታይ የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ እንደ አንድ የጋራ ፕሮጀክት (Joint venture) ግንባታና እድገት ጉዞ ልናየው እንችላለን፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያ “ሀ” ብለን ከመጀመሪያ ጀምረን ለመገንባት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በፕሮጀክቱ ባለቤትነትና መስራችነት እንዲሰለፉ አድርገናል፡፡ እንደማንኛውም ጥሩ የጋራ ፕሮጀክት ሁሉ ሁሉም ህዝቦች እኩል የመሳተፍ እድል ተሰጥቷቸው እንደየአቅማቸው ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ተደርጓል፡፡ አንዱ መስራች ሌላው ተጋባዥ ሆነው ሳይሆን ሁሉም በመስራችነት እኩል የመሳተፍ እድል ባገኙበት ሁኔታ የጀመሩት የጋራ ፕሮጀክት ነው፡፡ እኩል አስተዋጽኦ የማድረግ እድል ባገኙበት ሁኔታ ሁሉም ያላቸውን ሁሉ እንደአቅማቸው፣ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ንብረታቸውን አዋጥተዋል፡፡

በዚሁ አማካኝነት የጋራ ፕሮጀክቱ የሁሉንም አቅሞች አጣምሮ ስራ ከጀመረ በኋላ ሁሉም ባበረከቱት አስተዋጽኦ ልክ ከጥቅሙ ተጋሪ ይሆናሉ፡፡ ያለፈው ሂደት ተሽሮ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በአዲስ መሰረት ላይ ስትጀመር የዞሩ ዕዳዎችን ሁሉ አራግፋ ነው እየጀመረች ያለችው፡፡

ካለፈው ታሪክ በመነሳት ባዕድና ቤተኛ የሚባሉ ህዝቦች የሉንም፡፡ በዚህ ምክንያት ካለፈው የውርደትም ሆነ የገናናነት ታሪክ በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዳሴ የሁሉም ህዝቦች ህዳሴ፣ የሁሉም ህዝቦች የጋራ ፕሮጀክት ነው፡፡

የህዳሴው ባህሪ ከላይ የተጠቀሰው ነው ማለት ይህንኑ በማለታችን ብቻ እውን ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዞሩ ብድርና ዕዳዎችን ማወራረድ አለብን፡፡ ባዕድና ቤተኛ የሌለበት ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡ ይህንን በልዩ ህገ መንግስታችን አማካኝነት አረጋግጠናል፡፡ አሁን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የሆንነው ተገደን ሳይሆን ወደንና የጋራ ፕሮጀክቱ ተዋናይ መሆን አማልሎን ነው፡፡ አሁን ሁላችንም የፕሮጀክቱ መስራች አባላትና ቤተኞች ነን፡፡ ከእንግዲህ ያለፈውን ታሪክ መጠጊያ በማድረግ በተለየ ሁኔታ ቤተኛ ሆኖ ለመቀጠል የሚከጅል፣ ወይም በባይተዋርነት ውጭ ውጭ ማየት የሚከጅል ካለ በቂ ምክንያት ስላለው ሳይሆን አንድም የኪራይ ሰብሳቢነት መዥገር ስለሆነ፣ ወይም የነሱ ሰለባ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም ያለፈውን ሂሳብ አወራርደን መስራች አባላት ሆነን መጀመራችን አስፈላጊ ቢሆንም ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መስራች አባላት ብቻ ሳይሆን ለጋራ ፕሮጀክቱ አስተዋፅኦ የማድረግ እኩል እድልም ማግኘት አለብን፡፡

የአንደኛው ድርሻ ከአቅሙ በላይ፣ የሌላው ድርሻ ከአቅሙ በታች ከሆነ ፕሮጀክቱ በርግጥም የጋራ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ … ከሃያ ዓመታት በኋላ አሁንም ስለዞረው ድምርና እዳ የሚለፍፍ ብዙ ነው፡፡ ከሃያ ዓመታት በኋላም ያለፈውን ታሪክ የገናናነት ገፅታ ብቻ ወይም ያለፈውን ታሪክ የውርደት ገፅታ ብቻ በማጉላት ለመኖር የሚሻ፣ ህዳሴው ሁለቱን በሚዛናዊ መንገድ ከማጣመር ባሻገር በላይ በመሠረቱ አገሪቱን በአዲስ መሰረት ላይ የመገንባት አዲስ የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ለመቀበል የማይፈልግ ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ የህዳሴውና የጋራ ፕሮጀክቱን መርሆዎች የማይቀበል የተለየ ቤተኛ ለመሆን ወይም እንደነገረኛ ህፃን በልዩ ሁኔታ ማባበያ እንዳይለየው የሚፈልግም አልጠፋም፡፡ እናም የኢትዮጵያ ህዳሴ የተመሰረተባቸውን መርሆዎች ይዘትና ውጤት በሰፊው ማስተጋባትና ማሳመን ብዝሀነታችንን በብቃት የሚስተናገድበት ሥርዓት ለመፍጠርና በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ በዚህ ረገድ የነበሩብንን ውሱንነቶች ለዘለቄታው ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡…

የነኮሪያ ልማታዊ መንግስታት እኛ አሁን ካለንበት ሁኔታ ብዙም ከማይለይ የድህነት ደረጃ ተነስተው በሃምሳ አመታት ፈጣን የልማት ሂደት ከበለፀጉት አገሮች ጋር ለመሰለፍ ችለዋል፡፡ ልማታዊ መንግስታችንም ይህንን ግብ ማሳካት ይችላል፡፡ ይህንን የነታይዋን ልማታዊ መንግስታት በተግባር ያሳኩትና እኛም ልናሳካ የምንችለውን ግብ ነው የኢትዮጵያ ህዳሴ ብለን የምንጠራው፡

የነኮሪያ ልማታዊ መንግስታት ከተመሳሳይ ቦታ ተነስተው በተመሳሳይ ፍጥነት ተጉዘው ተመሳሳይ ግብ ላይ ለመድረስ 50 ዓመታት ከፈጀባቸው የአገራችንም የህዳሴ ጉዞ ተመሳሳይ ጊዜ ሊጠይቅ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ይህን የተፋጠነ ልማታዊ ጉዞ በተለምዶ አገሮች የሚፈረጁበትን መስፈርት መሰረት አድርገን ሂደቱን በሶስት ዋና ዋና ምዕራፎች ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ አገሮች ከድህነት አዙሪት መውጣት መቻላቸውን የሚያሳዩበትና ከድህነት ወደ ዝቅተኛው መካከለኛ ገቢ (lower middle income) የሚሸጋገሩበት ምዕራፍ ነው፡፡ ይህን ጉዞ ጀምረነዋል፡፡ የነብስ ወከፍ ገቢያችን በ100 ዶላር አካባቢ ከነበረበት ሁኔታ ተነስተን ወደ አንድ ሺ ዶላር አካባቢ ማለት ወደ ዝቅተኛው የመካከለኛ ገቢ የምንደርስበትን ጉዞ ለሰባት ዓመታት ያህል በተሳካ መልኩ ተጉዘናል፡፡ በያዝነው እጅግ ፈጣን ጉዞ መቀጠል ከቻልን የመጀመሪያውን ግብ ከአስር ዓመታት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ልንደርስበት እንችላለን፡፡ ሁለኛው ምዕራፍ አገሮች ወደ ከፍተኛው መካከለኛ ገቢ (upper middle income) ደረጃ የሚሸጋገሩበት የነብስ ወከፍ ገቢያቸው ከአንድ ሺ ወደ አምስት ሺ ዶላር አካባቢ የሚደርስበት ነው፡፡ ይህንን ጉዞ እጅግ በተፋጠነ ሁኔታ መፈፀም ከቻልን ከ15-20 ዓመታት ባለ ጊዜ ውስጥ መሻገር ይቻላል፡፡ የመጨረሻው ምዕራፍ አገሮች ከፍተኛ ገቢ ደረጃ ላይ የሚደርሱበት የነብስ ወከፍ ገቢው ከአምስት ሺ አካባቢ ወደ አስር ሺ አካባቢ የሚያደርሱበትና የመካከለኛ ገቢ አዙሪት እየተባለ የሚጠራውንና አገሮች ከመካከለኛ ገቢ ወደፊት መራመድ እንዲሳናቸው የሚይደርገውን ፈተና የሚያልፉበት ነው፡፡

ይህንኑም ጉዞ በተፋጠነ ሁኔታ ከሄድንበት በ15 ዓመታት አካባቢ መጨረስ ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር በጣም ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ጉዞን ማረጋገጥ ከቻልን የቀረንን የህዳሴ ጉዞ ከ40-45 አመት ባለ ጊዜ ውስጥ መጨረስ ይቻላል ማለት ነው፡፡

የህዳሴውን ጉዞ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመነሳትም ሆነ ባለፉት አመታት ያስገኘነውን ውጤት መሰረት ያደረገ ትንበያ በመጠቀም ስንገመተው የሚሰጠን ስዕል ተመሳሳይ ነው፡፡ ግባችን ላይ ለመድረስ ቢያንስ ከ40-45 ዓመታት ያስፈልገናል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ሁለት ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው፡፡ ፈጣን እድገቱ ሲቀጥልና፤ ፈጣን እድገቱ ያልተቆራረጠና ቀጣይነቱ የተረጋገጠ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ለአርባና ሃምሳ ዓመታት በተመሳሳይ ፍጥነት በተመሳሳይ አቅጣጫ መቀጠል እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰዎች ጉዞውን ሳይጀምሩ ቢታክታቸውና ተስፋ ቢቆርጡ የሚገርም አይሆንም፡፡ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ቆመናል ስንል ለእንደዚህ አይነቱ አስቸጋሪና አታካች ጉዞ ታጥቀን ተነስተናል ማለት ነው፡፡ ለአንድ ረጅም የማራቶን ሩጫ ሳይሆን በዱላ ቅብብሎሽ መልክ ለሚከናወኑ በርካታ የማራቶን ሩጫዎች ተሰልፈናል ማለት ነው፡፡ እንደማንኛውም የቅብብሎሽ ሩጫ ሁሉ ይህ የህዳሴ ጉዞ የለውጥም የቀጣይነትም ጉዞ እንደሚሆን ተገንዝበን ከለውጥ ሳንቦዝን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ውስብስብ ጉዞ ለመፈፀም ተዘጋጅተናል ማለት ነው፡፡”

የተሃድሶ መስመር እና የኢትዮጵያ ህዳሴ ህዳር 2003 አዲስ አበባ

Leave A Reply

Your email address will not be published.