የኢትዮጵያ መንግስት እይወሰዳቸው የሚገኙ የለውጥ እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተመድ ገለፀ

(ኢዜአ)- የኢትዮጵያ መንግስት አሁን እየወሰዳቸው ያሉ የለውጥ እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳቷም አድናቆቱን ገልጿል።

የኢፌድሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በየካቲት ወር ያወጣው የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ባሳለፍነው ቅዳሜ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ መወሰኑ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንቱ ጉባኤው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የቀረበውን ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ እስረኞች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ ማድረጉ የሚበረታታ የለውጥ እርምጃ ነው ብሏል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በህግ ጥላ ስር የነበሩ ፖለቲከኞችን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች እንዲፈቱ የተወሰነው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ነው ማለታቸውን በአብነት ጠቅሷል።

የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ዘይድ ራድ አል ሁሴን በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የዜጎች መብት እንዲጠበቅ አዲሱ የመንግስት መዋቅር የበለጠ ይሰራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መገንዘባቸውን ገልፀዋል።

የምስራቅ አፍርካ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በኢትዮጵያ የዜጎች መብት እንዳይጣስ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል የኮሚሽነሩ ቃል አቀባይ ራቪና ሻምሳዳኒ ተናግረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.