የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በፖለቲካ አለመረጋጋት በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ጉዳት ለሚደርስባቸው ንብረቶች የመድህን ዋስትና ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ

(አዲስ ዘመን)- የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ድርጅቱ በፖለቲካ አለመረጋጋት በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ለሚደርሱ የንብረት ጉዳቶች የመድህን ሽፍን አይሰጥም ነበር፡፡ አሁን ግን ከደንበኞች ተደጋጋሚና በርከት ያለ ጥያቄ በመቅረቡ ድርጅቱ ከአንድ ከዓለም አቀፍ የጠለፋ ድርጅት ጋር ስምምነት በማድረግ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ በግጭቶች ለሚደርሱ ጉዳቶች የመድህን ሽፋን ሊሰጥ ነው፡፡

የመድህን ሽፋኑን ለመስጠት ንብረቶች በግጭት ለሚከሰቱ አደጋዎች ተጋላጭነታቸው ምን ያህል ነው፣ ምን ያህል ጊዜ እንደሚከሰትና የሚወድመው ንብረት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መረጃዎችን የማሰባሰቡ ሥራ ከተሰራ በኋላ በመረጃው ላይ በመመስረት ከሦስት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጠለፋ ዋስትና ሰጪዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ድርድር መደረጉን አውስተው፤ ከሦስቱ ድርጅቶች አንዱን በመምረጥ የመድህን ዋስትናውን ለመስጠት ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ሚኒክሪ ከተባለው ዓለም አቀፍ የጠለፋ ዋስትና ድርጅት ጋር ባደረገው ድርድር መሰረት፤ አገሪቱ ውስጥ በግጭት ምክንያት በንብረት ላይ ጉዳት ቢደርስ ምን ያህል ሽፋን እንደሚሰጥ በጋራ በመወሰንና በውሳኔው መሰረት ህጎችንና ውሎችን በባለሙያዎች ተዘጋጅ ተው ለድርጅቱ መላካቸውን አውስተው፤ ድርጅቱ እነዚህን አጸድቆ መልሶ ሲልካቸው ለብሄራዊ ባንክ በማቅረብ የማጽደቅ ሥራ እንደሚሰራ አቶ ነጻነት ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ነጻነት ገለጻም፤ ድርጅቱ ቀሪ ሂደቱን እስከ ታኀሣሥ 30 ቀን 2010 .ም ድረስ በማጠናቀቅ ከጥር ወር ጀምሮ ፍላጎቱ ላላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች የመድህን ሽፋኑን መስጠት ይጀምራል።

ብዙ ደንበኞቻችን የመድህን ሽፋኑን ይፈልጋሉ ያሉት አቶ ነጻነት፤ በግጭቶች ምክንያት ለሚደርሱ የንብረት ጉዳቶች ሙሉ ለሙሉ ሽፋን እንዲያገኙ ፍላጎት ቢኖርም የአረቦን ክፍያ መጠኑ እጅግ ከፍተኛ ስለሚሆን የደንበኞችን አቅም መሰረት ባደረገ መልኩ ሽፋኑን እንደሚሰጥና በሽፋኑም በተለይ ተሽከርካሪዎች፣ ፋብሪካዎችና የአበባ እርሻዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ በግጭት ለሚደርሱ ጉዳቶች የመድህን ሽፍን የሚሰጥ ቢሆንም በእኛ አገር የሰላም ሁኔታ የተረጋጋ ስለነበርና የአረቦን ክፍያው በጣም ውድ ሆኗል። በዚህም የተነሳ በግጭቶች ለሚከሰቱ የንብረት ውድመቶች የመድህን ሽፋን አይሰጥም፡፡

የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በግጭት ምክንያት ለሚደርሱ የንብረት ጉዳቶች የመድህን ሽፋን የሚሰጠው ሚኒክሪ ከተባለ የጀርመን ዓለም አቀፍ ጠለፋ ዋስትና ድርጅት ጋር ሲሆን፤ ድርጅቱ የመድህን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም ከተለያዩ 10 ዓለም አቀፍ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ድርጅቶችና ከአገር ውስጥ የመድህን ሰጪ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ይሰራል ተብሏል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.