የኢትዮ-ጂቡቲ የጋራ የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ እየተካሄደ ነው

(ኢዜአ)- የኢትዮጵያና ጂቡቲ በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ የሚመክሩበት  24ኛው የጋራ የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት ሀገራትና ኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር መሃመድ ድሪል ስብሰባውን ሲከፍቱ  እንደተናገሩት የኢትዮ-ጂቡቲ የሁለትዮሽ ግንኙነት  በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ ከመምከር ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስራቸውን የሚያጠናከር ነው፡፡

የስብሰባው መድረክ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ኑሮ ለማሻሻል የሚረዱ ጠቃሚ የሃሳብ ልውውጥ  የሚደረግበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ህገ ወጥ  የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድ በመከላከል ረገድም የጋራ ድንበር ኮሚሽኑ አበረታች ስራዎች ማከናወኑን አመልክተዋል፡፡

መድረኩ የሁለቱ ሀገራት የእስካሁኑ ስኬቶች ይበልጥ የሚያጎለብቱና  የጋራ ችግሮቻቸው ለይተው የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ አምባሳደር መሃመድ ተናግረዋል፡፡

የጂቡቲ መንግስት ልኡካን ቡድን መሪ ሚስተር  ሱለይማን ኡመር አብዱልቃድር በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጂቡቲ  የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ይህም በማህበራዊ በባህልና በኢኮኖሚው መስኮች ይበልጥ ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በጂቡቲው  ዲኬል ከተማ በተካሄደው  23ኛው የጋራ ድንበር ኮሚሽኑ ስብሰባ ላይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አብሮነት የሚያጎለብት እንደ ትምህርት ፣ ጤናና  ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን ውሳኔ ማሳለፉን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ስብሰባም በድንበር ንግድ፣ በሁለቱ ሀገራት  መካከል በሚከናወኑ የእቃዎችና ሰዎች እንቅስቀሴ ሂደት የሚስተዋሉ  ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጠቃሚ ውሳኔዎች እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ገብረዮሃንስ ተክሉ እንዳሉትም ሁለቱ ሀገራትና ህዝቦቸ  ለረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ይህንን ግንኙነታቸውን በማጠናከር  ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እየተሸጋገሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ኮሚሽኑ ስብሰባ እስከ መጋቢት 6/2010ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ በተለያዩ አጀንደዎች ላይ እንደሚመክር ታውቋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.