የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል- ጠ/ሚ ኃይለማርያም

(ኤፍ ቢ ሲ)- የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚሲዮን መሪዎች እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ዲፕሎማቶች በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተቀመጠው መሰረት፥ በተመረጡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ባለሃብቶችን ማፈላለግ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ከዚህም ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያሳሰቡት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የማስፈፀም አቅሙን መገንባት እንደሚኖርበትና በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ፥ ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ ከሌሎች ከፍተኛ የምርምር ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት አለበት ብለዋል።

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት እቅስቃሴ በተመለከተ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች በአጠቃለይ ህብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው የኮሙዩኒኬሽን እና የህዝብ ዲፕሎማሲ ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በኢጋድ ጥላ ስር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሲዮን መሪዎች እና የመስሪያ ቤቱ የበላይ አመራሮች ነሀሴ 25 እና 27 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲሁም ከነሀሴ 28 አስከ ጳጉሜ 3 ቀን 2009 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ስበሰባ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

በስብሰባውም በተጠነቀቀው በጀት ዓመት በተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እና በ2010 በጀት ዓመት መከናወን በሚገባቸው አንኳር ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.