የእንግሊዙ ዊንች ኩባንያ በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ለመሰማራት ተስማማ

(ኢዜአ)- የእንግሊዙ ዊንች ኩባንያ በኢትዮጵያ 700 የገጠር መንደሮችን የፀሃይ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ተስማማ።

የውኃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ለሦስት ቀናት በእንግሊዝ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝታቸውም በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው የእንግሊዝ ኩባንያ ሥራ አስኪያጆች ጋር መወያየታቸውን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ በላከው መግለጫ ገልጿል።

በውይይታቸውም ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ኢትዮጵያ በመስኩ ያስመዘገበችውን ውጤትና በቀጣይ ምን ለመሥራት እንዳቀደችም ጭምር ለስራ አስኪያጆቹ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በውይይቱ የተሳተፉት እነዚሁ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ነው ያረጋገጡት።

በተለይም ዊንች የተሰኘው ኩባንያ በኢትዮጵያ 700 የገጠር መንደሮችን የከጸሃይ የሚመነጭ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ፈርሟል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የሰነቀችውን ግብ ለማሳካት የታዳሽ ኃይል ዘርፍ ቁልፍ አጀንዳ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለመኖሪያ ቤት የሚውል በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ከተቻለ የዜጎችን ህይወት መለወጥ እንደሚቻል ነው የተናገሩት።

ያም ብቻ ሳይሆን ለበርካቶች የሥራ እድል ይፈጥራል፤ የጤናና የትምህርትንም ውጤት እንዲሁ ለማሻሻል ያስችላል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል መስክ ያለውን እምቅ ኃብት በመጠቀም ለጎረቤት አገራትም ጭምር አቅርቦቱን ለማዳረስ እየሰራን ነው ብለዋል።

ይህም ለኢትዮጵያ ገቢ እንደሚያስገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዚህም የአንግሊዝ የመስኩ ስመ-ጥር ኩባንያዎችን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

የእንግሊዝ የዘርፉ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያሳዩት ፍላጎት የሚበረታታ ነው ያሉት ደግሞ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ናቸው።

በኢትዮጵያ በዘርፉ የግል ባለኃብቱ በስፋት እንዲሳተፍ አቅጣጫ መቀመጡ ለዘርፉ ቀጣይ እድገት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ የኢትዮጵያ መዕልዕክተኛ ጀርሚይ ሌፍሮይ በበኩላቸው  “የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ እቅድ አለው” ብለዋል።

የእንግሊዝ መንግሥትም በኢትዮጵያ የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ‘ኮርቢቲ ጂኦተርማል’ በሚለው መርኃ ግብር እየተሳተፈ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአሁኑ ጉብኝት አገራቱ በዘርፉ ያላቸውን አጋርነት ያጠናክረዋልም ብለዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.