የካንሰር በሽታን ለመከላከል ጥረቱ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርጋል – ፕሬዚዳንት ሙላቱ

(ኢዜአ)- የካንሰር በሽታን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ‘ፒፕልስ ቱ ፒፕልስ’ ከተሰኘ የኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ ማኅበርና ከማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ተወካዮች ጋር ትላንት በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በአገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የካንሰር ሕመም ለመከላከል ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ለመደገፍ መንግስት ዝግጁ መሆኑን የገለጹትም በዚሁ ጊዜ ነው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎች ለማቋቋም ያሰቡትን የልህቀት ማዕከል ለመጀመር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዲችሉ ተገቢው እገዛ ይደረጋልም ብለዋል ፕሬዚዳንት ሙላቱ።

ማኅበሩ በዘርፉ ያቀዳቸው ተግባራት ከአገሪቱ የጤና ስትራቴጂ ጋር የሚዛመዱና ጠቃሚ በመሆናቸው መንግስት በልዩ ትኩረት እንደሚያያቸው መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልፀዋል።

ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነው የ’ፒፕልስ ቱ ፒፕልስ’ ማኅበር ተወካይና የካንሰር ሐኪም ዶክተር እናውጋው መሃሪ ማኅበሩ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተሟላ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ለማቋቋም ማቀዱን ተናግረዋል።

ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረጉት ውይይት በዘርፉ የሰለጠኑ ኢትዮጵያዊያን የካንሰር ሕክምና ለመስጠትና አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ያካበቱትን ልምድ በአገር ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውንም ገልፀዋል።

“በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለመመስረት የታሰበው የልህቀት ማዕከል የካንሰር ሕክምናና ቅድመ መከላከልን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት ያቀደ በመሆኑ ስራው ሲጀመር ኢትዮጵያ ለሕክምናው የሚመጡባት አገር ልትሆን ትችላለች” ብለዋል።

የማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ በበኩላቸው ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የካንሰር መከላከያና መቆጣጠሪያ እቅድ በማውጣት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ክልሎች የካንሰር ሕክምናዎችን መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።

በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል ኅብረተሰቡ አመጋገቡን በማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን ማሻሻል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

እ.አ.አ በ1999 የተቋቋመው ‘ፒፕልስ ቱ ፒፕልስ’ የኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ማኅበር በመላው ዓለም ከ55 ሺህ በላይ አባላት አሉት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.