የኳታሩ አልጀዚራ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች አቅም ግንባታ ላይ የመሥራት ፍላጎቱን ገለጸ

(ኢዜአ)- የኳታሩ አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ በጋዜጠኞች የአቅም ግንባታና በሙያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ገለጸ።

በአልጀዚራው ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ሙስጠፋ ሶዋንግ የተመራ ልዑክ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ጋር መክሯል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ብቻ ሳትሆን የዲፕሎማቶች መዲና ናት ያሉት ዶክተር ሙስጠፋ አልጀዚራ በዘርፉ ባካበተው የረጅም ዓመታት ልምድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

አልጀዚራን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገው የሰው ኃይሉ ላይ በትኩረት መሥራቱ፣ ነፃና ተጠያቂነት የሚሰማው ጋዜጠኛ ማፍራቱና የፋይናንስ አቅሙን ማሳደጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

“አልጀዚራ ባለው ልምድ በተለይ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና ነፃ የመገናኛ ብዙኀንና የሰለጠነ፣ ተነሳሽነት ያለውና ለሙያው ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ ለማፍራት ከኢትዮጵያ ጋር የመሥራት ፍላጎት አለው” ነው ያሉት።

የልዑካን ቡድኑ ከዶክተር ነገሪ ጋር ባካሄደው ውይይት በፋይናንስ፣ በሙያዊ ስልጠናና በአቅም ግንባታ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ከስምምነት ደርሷል።

ዶክተር ነገሪ በበኩላቸው የአቅም ግንባታ ሥራው ለኢትዮጵያ ወሳኝ በመሆኑ አልጀዚራ ባለው የካበተ ልምድ አስፈላጊውን ድጋፍ  እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አልጀዚራ በተለይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር የጀመረውን ድጋፍ በሌሎች መገናኛ ብዙሃን አጠናክሮ እንዲቀጥልም እንዲሁ።

መንግስት መገናኛ ብዙኀን የራሳቸው የአቅም መገንቢያና የሥልጠና ማዕከላት እንዲኖሯቸው ያለውን ፍላጎትም ገልጸዋል ዶክተር ነገሪ።

የግሎቹን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የሙያው ፍላጎትና ተነሳሽነቱ ቢኖራቸውም የአቅም ግንባታ ክፍተቶች  እንደሚስተዋሉ ዶክተር ነገሪ ገልጸዋል።

በመሆኑም የአቅም ግንባታውን ክፍተት ለመሙላት ከአልጀዚራ ጋር የሚደረገው ትብብር ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አልጀዚራ ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ቢሮ በመክፈት ለአገሪቷ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ለአፍሪካ ኅብረት ኩነቶች ሽፋን በመስጠት ላይ ይገኛል።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ከአልጀዚራ ጋር መሥራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

እ.አ.አ በ1996 የተቋቋመው አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የሥርጭት ማዕከሉን በኳታር መዲና ዶሃ በማድረግ በተለይም በአፍሪካ፣ እስያና መካከለኛው ምስራቅ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.