የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ከሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሲላንዮ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ላንድ በባህል፣ በቋንቋ እና በታሪክ የሚገናኙ ህዝቦች አሏቸው ያሉ ሲሆን፥ ግንኙነቱን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ሶማሊ ላንድ የሰላም ማእከል ሆናለች ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፥ ሀገሪቱ ሌላ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ምርጫ እንደምታደርግ እምነት አለኝ ብለዋል።

ሶማሊ ላንድ የፊታችን ሰኞ ህዳር 4 ቀን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምታደርግ ሲሆን፥ በምርጫው ላይ ድምጽ ለመስጠትም ከ704 ሺህ በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል።

ምርጫው ሶማሊ ላንድ የምርጫ ስርዓት እድገትን ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሲላንዮ በምርጫው እንደማይካፈሉም ተነግሯል።

የሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሲላንዮ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት ከማንኛውም ሀገር በበለጠ ለሶማሊ ላንድ መንግስት እና ህዝብ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሁለቱ መንግስታት መካከል ያለው ትብብር አመርቂ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ትብብሩ ከዚህ በላቀ ደረጃ ክፍ እንዲል ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

በሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሲላንዮ የተመራው ልኡክ ከኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝቶ እንደሚወያይም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.