የዛሪማ ሜይዴይ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት 59 በመቶ መጠናቀቁን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለፀ

(ኤፍ ቢ ሲ)- የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት፥ 50 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለማው የዛሪማ ሜይዴይ ግድብ ግንባታ 59 በመቶ ደርሷል።

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በወልቃይት ወረዳ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ፥ የካቲት 2006 ዓ.ም ነው ግንባታው የተጀመረው።

የግድቡ ርዝመት 805 ሜትር ሲሆን ከፍታው 152 ሜትር፤ ውሃ የመያዝ አቅሙ ደግሞ 3 ነጥብ 497 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ነው።

ግድቡ የሚገነባው በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው የአስፋልት ኮር ሮክ ሂል (መሃል ለመሃል አስፋልት ኮር ያለው) ሲሆን፥ በአለት የሚሰራ ግድብ ነው::

3 ነጥብ 1 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ቱቦ ውሃ ከግድቡ ወደ መስኖ መሬት የሚወሰድ ሲሆን ቱቦውም 5 ነጥብ 5 ሜትር ዲያሜትር እና 50 ሜትር ኪዩብ ውሃ በሰከንድ የማሳለፍ አቅም አለው።

ሱር ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱን ግንባታ እያከናወነ ይገኛል።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች 2 የስኳር ፋብሪካዎች ሲሆኑ፥ ግንባታው በ2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የዛሪማ ሜይዴይ ግድብ አጠቃላይ ወጪው 15 ቢሊየን ብር መሆኑንም ነው የሚኒስተሩ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ የገለጹት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.