የዶ/ር ፍቅሬ የመፅሐፍ ዋነኛ ፖለቲካዊ ዓለማ እና አስገራሚ አንቀፆች

(አልአሚን ተስፋዬ) – ባለፈው ፅሑፌ የዶ/ር ፍቅርሬ ቶሎሳ መፅሐፍ በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ያስነሳውን ውዝግብ ለማሳየት መሞከሬ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ደግሞ የመፅሐፉ ዋነኛ ፖለቲካዊ ዓላማ እና ከመፅሐፉ አስገራሚ ናቸው ያልኳቸውን የተወሰኑ አንቀፆች ላካፍላችሁ ወድጃለሁ፡፡

ፍቅሬ ቶሎሳ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” የሚለውን መፅሐፍ ከፃፉ ሶስት እና አራት ዓመታት አስቀድሞ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስርዓት ለመቀየር እንደ ዋነኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ተደርጐ በልዩ ልዩ ሕትመቶች እና ሚዲያዎች ሲደጋገም የተደመጠው ሀሳብ “ አማራ እና ኦሮሞ” አንድ ላይ ግንባር ሲፈጥሩ ብቻ ነው ይህ ስርዓት ተወግዶ አዲስ ሥርዓት ሊፈጠር የሚችለው የሚለው አስተሳሰብ ነበር፡፡

ምንም እንኳ ይህ አስተሳሰብ በአብዛኛው የሚንፀባረቀው ስለ ኢትዮጵያ ሲያስቡ ሦስት ብሔሮች ላይ ማለትም አማራ ፣ ኦሮሞ እና ትግራይ ላይ ትኩረት በሚያደርጉ የከተማ ፖለቲከኞች ዘንድ ቢሆንም አንዳንድ ምራቃቸውን የዋጡ ናቸው የሚባሉ ምሁራንም የዚሁ አስተሳሰብ ሰለባ መሆናቸውን የሚያንፀባርቅ ፅሑፍ ቃለ-ምልልስ እና መግለጫ ሲሰጡ መታየታቸው አልቀረም ነበር፡፡

ከነዚህ ጐምቱ ግለሰቦች መካከል ሁልጊዜም በአወዛጋቢ አስተያየታቸው እና አማራ የሚባል ሕዝብ የለም በሚል ንግግራቸው የሚታወቁት ፕ/ር መስፋን ወልደማርያም ሰኔ 2007 ዓ.ም በታተመው አሻራ ቁጥር 2 መፅሔት ላይ ኢትዮጵያ አሁን ከገባትበት አዘቅት ለመውጣት የሚያስፈልጋት መፍትሔ ምንድን ነው በሚል ለቀረበላቸው አስተያየት በሰጡት ምላሽ “ከዚህ አዘቅት የሚያወጣን ላልከው የህብረተሰቡን 70 በመቶ ያህል የሚሸፍኑት የኦሮሞ እና የአማርኛ ተናጋሪ ክፍሎች አደጋው ታይቷቸው አንድ አይነት ስምምነት ላይ መድረስ ከቻሉ መድህን ማምጣት አይከብዳቸውም የሚል እምነት አለኝ” አሉ፡፡

ይህን ተከትሎ በሚወጡት መፅሔቶች እና መፃህፍቶች ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎች ሰማኒያ የሚጠጉ ብሔር ብሔሰቦች መኖራቸውን ከግምት የማያስገቡ “ከእኔና አንቺ በቀር እነማን ነበሩ” የሚሉ ድምፆች መስተጋባት ጀመሩ፡፡ የፕ/ር መስፍን የመዶለት ባህሪ በሌላ ፅሑፌ የምመለስበት ቢሆንም የፍቅሬ ቶሎሳ መፅሐፍ መውጣትን ተከትሎ ደራሲው ለአዲስ አድማስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ስለ እውነተኛ ፀሐፊነቱ እና ብቃቱ በፕ/ር መስፍን የተመሰከረለት እና የእሳቸው አይዞህ ባይነት እንዳልተለየው መጥቀሱ የመፅሐፉን ፖለቲካዊ አላማ ፍንትው ብሎ እንዲታየን በር ከፋች ንግግር ነበር፡፡ በእርግጥም በኦሮሞ እና በአማራ “እውነተኛ የዘር ምንጭ” ላይ ትኩረት ያደርጋል የተባለው መፅሐፍ ሁለቱ ህዝቦች ከአንድ አባት የተገኙ ኩሻዊ ህዝቦች መሆናቸውንና የትግራይ ህዝብ ግን ከነሱ በኋላ ከኢራቅ “ትግሪስ” ከተባለ ቦታ የመጣ ሴማዊ ህዝብ ነው ብሎ መነሳቱን ስንመለከት በመፅሐፉ ደጋፊነት እና አድናቂነት የተሰለፉት “ከኔ እና አንቺ በቀር” የተሰኘው ዜማ አቀንቃኞች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እኛ ከተስማማን ሌላው ብሔር ብሔረሰብ ምንም የማያመጣ ደካማ ስብስብ ነው ብለው የሚያምኑ ፖለቲካዊ አላማ ያነገቡ ኃይሎች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡

መፅሐፉ የታተመበትን ሁነኛ ወቅት እና በወቅቱ ይጐሰም የነበረውን “የኦሮሞ እና የአማራ አመፅ” የሚል መፈክር ጋር ስናሰናስለው መፅሐፉ ምንም እንኳ ከታሪክ መፃህፍትነት ይልቅ ወደ ታሪካዊ ልብ ወለድነት የሚያመዝን ቢሆንም ሊያሳካ ካሰበው ፖለቲካዊ አላማ አንፃር ግርግሩን የማዳመቅ ኃላፊነት አልተወጣም ማለት አይችልም፡፡ እዚህ ላይ እንኳን የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች የዓለም ህዝብ ከአንድ የዘር ምንጭ ነው (ከአዳምም ይሁን ከሉሲ)የተገኘው ማለት ተገቢ እና የሚደገፍ ሀሳብ መሆኑ ባይካድም ከእኔና አንቺ በቀር ሌሎቹ ከሌላ ነው የተገኙት በሚል አኳኋን መምጣቱ የመፅሐፉ ዋነኛ አስከፊ እና ሩቅ የማያስኬድ በጊዜያዊ የፖለቲካ ሆይ ሆይታ የተሞላ ባህሪ መሆኑን መግለፅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ለማንኛውም ከመፅሐፉ ካስገረሙኝ እና አንዱ ምሁር ነኝ የሚል ሰው እንዴት እንዲህ በመሠለኝ እና በደስ አለኝ ሊፅፍ ይችላል ያስባሉኝ ጥቂት አንቀፆች እንድታነቡ በመጋበዝ የዛሬ ፅሑፌን እዘጋለሁ፡፡

“ዘአንዳቤት ወይም ቤተ እንዳ መጽሐፍት በእጅ የሚቀዱበት ቦታ ሲሆን በዚያን ጊዜ በእጅ የሚገለበጠው መጽሐፍ ጥራቱ በማተሚያ ቤት የሚታተመውን ያስንቅ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ምናልባት ያም ሰው በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በአዲያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግስት ያንኑ አንድ ቅጂ ይዞ ወደ ተለመደው አገር ወደ ኑቢያ ተሰዶ ይሆናል፡፡ አለዚያም መፅሐፉ በሌላ ሰው ወደዛ ተወስዶ ለኛ ለተተኪዎቹ ትውልዶች ይደርስ ዘንድ ከአንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ ጎን ከሚገኝ ከትልቅ ቁዋጥኝ ከተፈለፈለ አለት ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ቤተ ክርስቲያኑ በአረብ ሙስሊሞች ሲቃጠል መጽሐፉ አለቱ ውስጥ ተረፈ፡፡ ያንን መጽሐፍ ነው መሪራስ አማን በላይ አግኝቶ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው፡፡ የብራና ጥቅሎቹ የተፃፉት በግዕዝ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣልንና የእውነተኛው ታሪካችን ብርሃን እንደገና እንዲበራ ያደረገልን መሪራስ አማን በላይም ባለውለታችን ነው፡፡ በመሆኑም ምስጋና ይገባዋል፡፡

መሪራስ አማን በላይ በመጽሐፈ ሱባኤ ውስጥ ተካትተው ካገኛቸው መፃሕፍት ውስጥ በትልቁ ነብይ በሄኖክ የተፃፈውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የሠራዊት ጌታ ጦርነቶች መጽሐፍ”በሚል የተጠቀሰው ስለ ዓለም አፈጣጠር የሚተርከው “መጽሐፈ ጃን ሸዋ” ይገኝበታል፡፡ ሙሴ ከአማቱ ከጄትሮ (ዮቶር- አብ) ጋር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በነበረበት ወቅት በእኛ እጅ የነበረውን ይህን መጽሐፍ አግኝቶ ነው “ኦሪት ዘ ፍጥረት” የተሰኘ መጽሐፉን ከኛው መፅሐፍ ላይ ቀንጭቦ የፃፈው፡፡ …..”(ገፅ 9-10)

“ሚያዚያ 5 ቀን505 ዓ.ም የተወለደው ቅዱስ ያሬድ (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዜማ ደራሲ ማህሌታዊ ያሬድ) በቅድመ አያቱ ኦሮሞ ከሆነች መደባይ ይወለዳል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በአባቱ በኩል የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆነ አንድ ዘመዱም መደባይ/ኦሮሞ ነው፡፡ አክሱም አጠገብ መደባይ የተባለ ቦታ ተገኝቷል፡፡ ያሬድ አክሱምን ከለቀቀ በኋላ እናቱ ወደምትኖርበት ወደዚህ መደባይ ወደ ተባለው ቦታ ነው የሄደው፡፡” (ገፅ 47)

“ስለ ደሼት ስንናገር ምንም እንኳን ተረት ቢመስልም ሀቅ ስለሆነውና ለየት ስለሚለው ውልደቱ መናገር ጠቃሚ ነው፡፡ የቤላም (በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው እናቱ ነቢይትዋ ሼምሼር መነኩሲት ነበረች፡፡ ከወንድ እርቃ በግዮን አካባቢ በገዳም ውስጥ መንፈሳዊ ህይወት ትመራ ነበር፡፡ አንድ ቀን በግዮን ወንዝ ሳይሆን አይቀርም ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር በማህፀንዋ ዘልቆ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ፡፡”(ገፅ 60)

“በቅርቡ ያገራችን ታሪክ በአድዋ፣ በማይጨውና በደፈጣ ውጊያ ጦርነቶች እንኩዋ ለዚች ሰንደቅ ዓላማ ከተፋለሙ ኦሮሞዎች ጥቂቶቹን ለማስታወስ፣ የአፄ ምኒልክ ባለቤት ንግስት ጣይቱ ብጡል ፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ፊታውራሪ ባልቻ አባ-ነፍሶ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ እና ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ እና ወይዘሮ ልክ የለሽ በያን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡” (ገፅ 131-132)

“ጌታ እየሱስ ክርስቶስ እሥራኤል ውስጥ ራሱን ለአይሁድ ከመግለጡ በፊት እድሜው ከ22 እስከ 25 ዓመት በነረበት ወቅት ለ3 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ እንደነበር የተፃፈ ዜና ማርሄሐ የተባለ ማስረጃ ተገኝቷል፡፡ በኋላም በርቶሎሚዎስ፣ ማቲዎስ፣ ማትያስ፣ ናትናኤል፣ የእልፋዎስ ልጅ ያዕቆብ እና ቶማስ የተባሉ 6 ደቀ መዛሙርቱን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል፡፡

እየሱስ ክርስቶስ በቤተ- ልሔም ሲወለድም ልደቱን ሲጠባበቁ የነበሩ 12 የኢትዮጵያ ጠቢባን ንጉሦች የአማራን፣ የኦሮሞን፣ የአፋርን፣ የሶማሌን የኑብያን እና የሌሎቹንም የኢትዮጵያ ጎሳዎች ወክለው ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ሰግደውለት ስጦታ አበርክተውለታል፡፡”(ገፅ 183)

“የአማራን ትክክለኛ ማንነት በተመለከተ አንዳንድ የአውሮፓ ምሁራን ተብዬዎች እንደሚሉት አማሮች ሴማውያን አይደሉም፡፡ ኦሮሞና አማራ ካንድ ምንጭ ነው የተቀዱት፡፡ ቀደም ሲል እንደተረጋገጠው ኦሮሞና አማራ በዘርም አንድ ናቸው፡፡ ኦሮሞዎች ኩሻውያን ከሆኑ አማሮች እንዴት ነው ሴማውያን የሚሆኑት አንድ ሰው ቋንቋቸውን ሴማዊ አድርጎ ስለመደበው አማሮችም ሴማውያንም ተደርገው የሚመደቡ ከሆነ ግልብ ምዳባ ነው፡፡” (ገፅ 246)

Leave A Reply

Your email address will not be published.