የግብፅ ኩባንያ በ120 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን ሊገነባ ነው

(አዲስ ዘመን)- በኤሌክትሪክና በንፋስ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ የተሰማራው የግብፁ ኩባንያ ኤልስዌዲ በ120 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን ሊገነባ መሆኑ ተመለከተ፡፡
ድርጅቱ የኢንዱስትሪ ዞኑን ለመገንባት ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ማቅረቡን በኢትዮጵያ የሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡ ጥያቄው ምላሽ እንዳገኘም ቀጣይ ሂደቱ እንደሚጀመር ነው የተገለጸው፡፡
የኢንዱስትሪ መንደሩ መገንባት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ከማገዙም በላይ የግብፅ ባለሀብቶችን ለመሳብም እንደሚረዳ ኤምባሲው አስታውቋል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በመድኃኒት፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና በእንስሳት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ያልማሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የግብፅ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን በተለይም በመድኃኒት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር የመመካከር ዕቅድ እንዳላቸው ነው የተገለፀው፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ ሆስፒታል የመገንባት ፍላጎት እንዳላትም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግብፅ ባደረጉት ጉብኝት በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ከግብፅ ባለሀብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ እአአ በ2014 በኢትዮጵያ የግብርና ማቀነባበሪያ ለማቋቋም ከስምምነት መድረሳቸውን መረጃው ያትታል፡፡ በተያዘው ዓመት ስምምነቱን ወደ ተግባር ለማስገባት የግብፅ ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መሪዎች ውይይትና ምክክር አድርገዋል፡፡ በዚህም ሶስቱ አገራት በጋራ ልማቶች ዙሪያ እንደ አንድ አገር የማሰብ አቋም መያዝ እንዳለባቸው አረጋግጠዋል፡፡ በየአገራቱ ለሚከናወኑ መሰረተ ልማቶችም ድጋፍ የሚያደርግ የመሰረተ ልማት ፈንድ እንዲቋቋም ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.