የጥድፊያ ትውልድ (ከአነበብኩት)

እመጓ ፣ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ, 2008

(ሸጊት ከድሬ ) – “በአፍላ ትጀምራላችሁ የወረት ትተውታላችሁ፡፡ ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ፤ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤ የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤ የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ፡፡ ምኞታችሁ ልክ የለውም፤ አምሮታችሁ ብዙ ነው፡፡ የአማራችሁን ስታገኙ ወዲያው ይሰለቻችኋል፡፡ ተዉ የተባላችሁትን ትሽራላችሁ፤ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፤ የተፈቀደላችሁን ችላ ትሉታላችሁ፡፡ ቤተመቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደፊት ቤተ መቅደሱን በመስታዎት ሠርታችሁ መቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከውጪ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ፡፡ ሁሉ አላችሁ፤ ግን ባዷችሁን ናችሁ፡፡ ሃይማኖት እንጂ እምነት “መድኃኒት ነው ያልከው? መቀመሚያውን ነግሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ትተኸኝ ትሄዳለህ፡፡ ጥበብን “ሀ ግእዝ” ብዬ ላስተምርህ ብሞክር፣ መንደር ውስጥ በቃረምካት ዕውቀት ተመክተህ በመሰልቸት “ሆ ሳብዕ” ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ፡፡ የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተለከፈከፈ የተማሪ ኮፋዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል፡፡ ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ፣ ሰርታችሁ ሀብት ስታፈሩ፣ ከላይ የሆናችሁበትን ሀገር ለቃችሁ፣ ሰፋ ወዳለው እንሂድ ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ፡፡ ትቀጥላላችሁ፤ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ፡፡ ችኰላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ፡፡ በጽኑ ታማችኋል፡፡

ከታሪክ ፍቅርንና ልማትን ሳይሆን ጥላቻንና ጥፋትን ለይታችሁ ትቆፍራላችሁ፡፡ ከዚያም ቀጥላችሁ የከበረ ማዕድን እንዳወጣችሁ ሁሉ በኩራት ደረታችሁን ነፍታችሁ ሳትመርጡ ሁሉን በአደባባይ ትዘሩታላችሁ፤ እናም ወደ ኋላ ስለታሪካችሁና ስለ ቅርሳችሁ ባሰባችሁ ቁጥር ፍርሃትና ሃፍረት ይሰማችኋል፡፡ ስለሆነም ከኋላ ታሪካችሁና ክብራችሁ እየራቃችሁ መጣችሁ፡፡ የአሸናፊነትንና የተሸናፊነትን ትርጉም በአንድ ላይ የያዙ ሃውልቶችን ታቆማላችሁ፡፡ ለግልጽነትና ለነፃነት እያላችሁ በምታደርጉት ሽኩቻ ዕርቃን ወደመሆን ወረዳችሁ፡፡

ቅቤ ላይወጣችሁ ትናጣላችሁ፡፡ በዚህ ዓለም ጥድፊያ ታማችኋል፡፡ ሀገራችሁን ትንቃላችሁ፤ ጥላችሁ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ፤ ከሄዳችሁ በኋላ ደግሞ አፍታ ሳትቆዩ አገሬ ናፈቀኝ ትላላችሁ፡፡ በቁማችሁ የናቃችሁትን የሀገራችሁን አፈር በሞታችሁ ልትለብሱት ትናፍቃላችሁ፡፡ “ለሀገሬ አፈር አብቃኝ” ብላችሁ በድናችሁን ልካችሁ የወገኖቻችሁን ልብ ትሰብራላችሁ፡፡ ግብዝነታችሁ መጠን የለውም፡፡ ሁለት ሀገር እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ፤ አንዱን በደም ሌላኛውን በመታወቂያ ታስባላችሁ፡፡ ከአንዱም ግን በአግባቡ አትኖሩም፡፡ ዘመናችሁም በምልልስና በመዋተት ያልቃል፡፡ ምን እንደምትፈልጉ አታውቁም እናም ፍለጋችሁ አያልቅም፡፡

በዚህ የተነሣ ምሥጢር ለመካፈል ቅርስ ለመረከብ የሚያስችል ሰብእና አልገነባችሁም፡፡ እኛ የመገናኛውን ድልድይ ስላልሠራንና ከእናንተ ስለራቅን ሳይሆን ስለማይታዩት ወይም ማየት ስለማትፈልጉ አለበለዚያም እንደ ልቦለድ ገጸ ባህርይ የራሳችሁን ያሸበረቀ አስረካቢ ፈጥራችሁ እውኑን ሳይሆን ምናባችሁን መረከብ ፈልጋችሁ ስለምታጡት ነው፡፡ እኛ ደግሞ እናንተ ታዩን ዘንድ አላሸበረቅንም፤ ማሸብረቅም አንፈልግም፡፡ በዚህ ምክንያት ለእናንተ ምስጢር ለመንገር፣ ቅርስ ለማውረስ እጅግ ከባድ ሆኗል፡፡ እኛ አባቶቻችንን እናምናለን፡፡ በእነርሱም ደስ ይለናል፡፡ የነገሩንን ተቀብለን ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀን እንኖራለን፡፡

“ጽላተ ሙሴ አክሱም ጽዮን እንዳለች ሲነግሩን መጋረጃ ገልጠን፣ ሳጥን ከፍተን እንይ አላልንም፤”

ጌታ የተሰቀለበት የግማደ መስቀሉ ክፋይ ግሼን ማርያም አለ ሲሉን ቆፍረን አውጥተን እንመልከት አላልንም፤

ቅዱሱ ጽዋ መንዝ ውስጥ አለ ሲሉንም ዋሻ እናስስ አላልንም፡፡

አባቶቻችንን አምነን፣ ሀገራችን የበረከት ምድር መሆኗን ተረድተን፣ የጌታችንን የጸጋ ስጦታ ተቀብለን በእምነት እንኖራለን፡፡ ምንም የለንም፤ ሁሉ ግን የኛ ነው፡፡ ድሆች ብንባልም ባለጸጎችም ነን፡፡ የተራቆትን ብንመስልም የፀጋ ልብስ አለን፡፡ ሐዘንተኞች ብንመስልም ደስተኞች ነን፡፡ ስለ ሀገራችን መባረክ፣ ቅድስት ሀገር መሆን፣ ቅዱስ ቅርስ በእጃችን እንዳለ ዓለም እንዲያረጋግጥልን አንፈልግም፡፡ የሌለንን አለን፣ ያልተሰጠንን ተቀበልን ብለን የምንኮፈስ ግብዞችም አይደለንምና፡፡ የሌለን ነገር ለመጠበቅና ለመታመን ስንል ሥጋችንን እየጎሰምን በገዳም ለመኖር የምንወስን ጅሎችም አይደለንምና፡፡

አንተ ደግሞ ፍለጋው የማያልቀው የዚህ ትውልድ ናሙና ነህና አምነህ ሄድ ብልህ አትቀበለኝም፡፡ እንደ ቶማስ በዐይንህ ካላየህ፣ በእጅህ ካልዳሰስከው አትረካም፡፡ የትውልዱ ሕመም ይህ ነው፡፡ አንተም የዚህ ህመም ተጠቂ ትውልድ ምሳሌ ነህና ጫፉን ነግረንህ በእምነት እንድትኖር ችላ ብንልህ እንኳን ፈልፍለህ ለማወቅ ትዳክራለህ፡፡ ያወቅከውን ደግሞ ትዘራዋለህ፡፡ አንተ የትውልዱ ጥሩ ናሙና ነህ፡፡

አንተን ሊያቆምህ የሚችለው የመንገዱ ማለቅ ብቻ ነው፡፡ ሩቅ መንደገኛ የሚያቆመው አንድም መንገዱ ሲያልቅ አለበለዚያ መንገደኛው ራሱ ሲያልቅ ነውና፡፡

አንተ የተጓዝከውን ገና ብዙዎች ይጓዙታል፡፡ ያወቅከውንና የደረስክበትንም መፃፍህ ስለማይቀር ያን ተከትለው ብዙዎች ይጓዛሉ፡፡ ግን ልብ በል ብታገኙትም አታምኑም፡፡ እርሱ ራሱ ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለ ትላላችሁ፡፡ አንተ በነገርካቸው መሠረት ሌሎች ካላመኑልህ ደግሞ አንተም እምነትህ ይካዳል፡፡ ራሳችሁንና የራሳችሁን እውነት የምታረጋግጡት በምዕራቡ ዓለም መለኪያ ብቻ ነውና፡፡”

እመጓ ፣ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ, 2008

Leave A Reply

Your email address will not be published.