የፀረ-ሙስና ትግሎ ቀጥሏል

ከሰሞኑ በከፍተኛ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በህግ እየታዩ ያሉት የመንግስት ሹመኞች፣ ደላሎችና ባለሀብቶች ንብረት ላይ ፍርድቤት እገዳ ጣለ። የፍርድ ቤት ማስረጃዎች እንደሚያመላከቱት የንብረት እገዳው የተጣለው በተጠርጣሪ ወንጀለኞቹ እና ህገወጥ ገንዘቡን ለማሸሽ ሲሉ በደበቁባቸው የቤተሰብ አባላቶቻቸው ጭምር ነው። አስከአሁን ድረስ የታገደው የግለሰቦችና የተቋማት ብዛት 210 እንደሆነ ታውቋል።

ከታገዱት የኩባንያዎች ንብረት መሃከል ባለ 5 ኮከቡ የኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት የሆኑት የአቶ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ድርጅት አንዱ ሲሆን ግለሰቡ የፀረ-ሙስናው ክስ ከመቅረቡ ከቀናት በፊት ከሃገር መውጣታቸው ታውቋል። ከገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ድርጅት በተጨማሪም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ድርጅቶች ንብረቶች ታግደዋል።

– አሰር ኮንስትራክሽን
– ቲና ኮንስትራክሽን
– ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን
– የማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ
– ትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ትሬዲንግ
– ሀይሰም ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማህበር
– ከማኒክ ትሬዲንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር
– ጆንግ ሊንግ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

የእነዚህ ድርጅቶች ንብረት መታገድ ዋናው ምክንያት ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በህገወጥ መንገድ የዘረፉትን ሀብት እንዳያሸሹ መሆኑ ይታወቃል።

ትላንት በዋለው ችሎት ላይ የቀድሞው የአ/አ መንደዶች ባለስልጣን የነበሩት ኢንጅነር ፍቃዱ ሃይሌ ለወርሀዊ ምግብ አስቤዛ በማለት እቤቴ አስቀምጨው የነበረውና ፖሊስ በኢግዚብትነት የያዘው ገንዘብ ለቤተሰቤ ይመለስልኝ በማለት ጠይቀው ነበር። የኢንጅነሩ ቤት ሲበረበር ተይዞ የነበረው 800,000 የኢትዮጵያ ብርና 11,000 ገደማ የአሜሪካ ዶላር መሆኑ የግለሰቡን ጥያቄ አስገራሚ አድርጎት ነበር።

ከወደ ፍርድቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ከአሁን ቀደም ከነበሩት ክሶች በእጅጉ በላቀ ሁኔታ ፖሊስና አቃቤህግ የሰሞኑን ተጠርጣሪ ወንጀለኞቹን ከማሰራቸው በፊት በጣም በተደራጀ ሁኔታ መረጃዎችን ማደራጀታቸውን ነው። መንግስትም ይህንን የፀረሙስና ትግል በቀጣይም አጠናክሮ እየቀጠለ እንደሆነ ይነገራል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.