የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የሚሰጠውን ነጻ የህግ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ስራ ሊገባ ነው

(ኤፍ ቢ ሲ)- የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አረጋውያንን ጨምሮ አቅም ለሌላቸው ዜጎች የሚሰጠውን ነጻ የህግ ድጋፍ ደረጃውን የጠበቀ እና ተደራሽ ለማድረግ ስትራቴጂ ነድፎ በዚህ አመት ወደ ስራ ሊገባ ነው፡፡

ከሃገሪቱ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚልቁት አረጋውያን መሆናቸውን ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከእነዚህ አረጋውያን መካከል ታዲያ አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ አቅም ችግር ያለባቸው እና ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተጋላጭ እንደሆኑ ይነገራል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ደግሞ አረጋውያኑን ጨምሮ የመብት ጥሰት የሚያጋጥማቸው እና አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህግ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ተቀምጧል።

ይህ አይነቱ ነጻ የህግ አገልግሎት አረጋውያኑ ፍትህ እንዲያገኙ ከመርዳቱም ባሻገር ከተለያየ እንግልት እንዳዳናቸው ይናገራሉ።

አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በህግ ጉዳይ ላይ ከሚሰሩ ዘጠኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በአመት በአማካይ ከ29 በላይ የህግ ጉዳዮችን እንደሚያስተናግድ የጠቀሰው ኮሚሽኑ፥ በተለይ አቅም ለሌላቸው አረጋውያን በሚሰጠው የህግ ድጋፍ በርካቶችን ተጠቃሚ እያደገ መሆኑንም ነው የገለጸው።

አገልግሎቱን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግም በሃገር አቀፍ ደረጃ በተደራጁት ስምንት አዳዲስ ቅርንጫፎቹ በኩል አገልግሎቱን ለማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን፥ በፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የህግ ጥናትና ማስረጽ አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸዉ ወርቁ ተናግረዋል።

በአጠቃላይም በህግ ድጋፍ ላይ ሊሰሩ የሚችሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በማካተት ወጥ በሆነ አሰራር የነጻ የህግ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አሁን ላይም የተሳታፊ አካላት ስፋት፣ ደረጃ እና ፍቃድ አሰጣጥ ላይ ወጥ የሆነ አሰራርን በማስቀመጥ ተደራሽነት እና ጥራትን ማስፋት የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፎ በተያዘው በጀት አመት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.