ግማሽ ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባው የሰመራ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ተመረቀ

(ኤፍ ቢ ሲ)- በሰመራ ከተማ ከ450 ሚሊየን ብር በላይ የተገነባው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ ተመርቋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ስያሜ፥ “ሱልጣን አሊሚራህ አንፎሬ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ እንዲጠራም ተወስኗል።

አውሮፕላን ማረፊያው የአውሮፕላን መንደርደሪያ እና የመንገደኞች ተርሚናል እንደተገነባለት ተገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሀጂ ስዩም አወል እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሃመድ ረሺድ በተገኙበት ነው የአውሮፕላን ማረፊያው የተመረቀው።

ግንባታውን አፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ያካሄደው ሲሆን፥ ከተቀመጠለት የግንባታ ማጠቃለያ ጊዜ አስቀድሞ ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በማድረሱ በሶስቱም የስራ ሃላፊዎች ምስጋና ቀርቦለታል።

አውሮፕላን ማረፊያው ወደ ስራ መግባቱ የክልሉን የመስኖ እና ማዕድን ልማት ኢንቨስትመንት ለማሳለጥ እንዲሁም ከጅቡቲ ጋር በቀላሉ ለመገናኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልፀዋል።

ከገቢ እና ወጪ ንግድ ጋር የሎጅስቲክስ ስርዓቱን በማዘመን ረገድ የሚጫወተው ሚናም ቀላል አይደለም ነው የተባለው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.