ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙ ንዑስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣብያዎች በታህሳስ ይጠናቀቃሉ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙ 21 ንዑስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማሻሻያ እና አዳዲስ ግንባታዎች በታህሳስ ወር ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድርና ዕርዳታ ግንባታቸው ሲከናወን የቆየው እነዚህ ፕሮጀክቶች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ግንባታው 21 ንኡስ ጣቢያዎችና 943 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማሻሻያ እና አዳዲስ ግንባታንም ያካትታል።

የማሻሻያ ግንባታዎቹ በመላ አገሪቷ እየተከናወነ ሲሆን፥ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን የሚያሰፉ እና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ጭምር ኃይል የሚያቀርቡ ናቸው ተብሏል።

በድርጅቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ውድነህ የማነ እንደተናገሩት፥ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቁና በአገሪቷ የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ማቃለል የሚያስችሉ ናቸው።

አቶ ውድነህ፥ ከቆቃ – ሁርሶ – ድሬደዋ – ጂቡቲ የሚዘልቀው፣ ከወልቂጤ – በሆሳና – ሃላባ አድርጎ ለአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚደርሰውና ከአላማጣ – መኾኒ – መቀሌ የሚዘልቀው መስመር ሥራው እየተፋጠነ መሆኑን እንደማሳያ አንስተዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሌብ ወጋሮ በበኩላቸው ባንኩ በቀዳሚነት ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛው ነው ብሏል።

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ በመቻላቸው እና የተፈቀደው ገንዘብም በአግባቡ ሥራ ላይ በመዋሉ፥ ባንኩ በቀጣይ አገሪቷ ለሌሎች የኃይል ፕሮጀክቶች የምትፈልገውን ገንዘብ እንዲፈቅድ ያስችለዋል በማለት አስታውቋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.