ፓርላማው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማብራሪያ ጠራ

(ሪፖርተር )- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ ወቅታዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ጥሪ ማቅረቡ ተሰማ።

ምንጮች እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመጪው ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ተገኝተው ከሕዝብ ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ጠይቀው ተቀባይነት ካላገኙ በስተቀር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማውን ጥሪ ተቀብለው መገኘትና ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ አለባቸው።

የምክር ቤቱ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጧቸው የፈለጉበት ዋነኛ ጉዳይ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰብስቦ ባሳለፋቸው ሁለት መሠረታዊ ውሳኔዎች ላይ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ በሙሉ መቀበሉና የልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑ አይዘነጋም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.