ፓርቲዎች በምርጫ ሥርዓቱ የመቶኛ ድርሻ ስምምነት ላይ ደረሱ

(ሪፖርትር)- ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና የአገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር ፓርቲዎቹ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ እንዲሆኑ በመስማማታቸው፣ 80 በመቶው በአብላጫ 20 በመቶው ደግሞ በተመጣጣኝ እንዲሆን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ከዚህ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት ላይ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ የቅይጡ መቶኛ ድርሻ ላይ ግን ሳይስማሙ ድርድሩን በቀጠሮ ሲያዘገዩ ቆይተው ነው ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ ድርድሮች ኢሕአዴግ መጀመርያ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ላይ 90 በ10 የመቶኛ ድርሻ እንዲኖረው እንደሚፈልግ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በመቀጠልም 85 በ15፣ እንዲሁም መጨረሻ ላይ 80 በ20 በማቅረብ የመጨረሻው እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡

ከተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ለድርድሩ ዓላማ ሲባል ኅብረት የፈጠሩት 11 ፓርቲዎች መጀመርያ 50 በ50 እንዲሆን አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በመቀጠልም ወደ 40 በ60 ዝቅ አድርገው እንደነበርና ይህንኑ አቋማቸውን እንደማይለውጡ ገልጸው ነበር፡፡ ሆኖም በመጨረሻ በኢሕአዴግ የቀረበውን የ80 በ20 የመቶኛ ድርሻ ተቀብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት የአብላጫና ተመጣጣኝ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት በፌዴራል ፓርላማ፣ በክልል ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ የደረሱበት ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት፣ አሁን ካሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች በተጨማሪ 110 መቀመጫዎች እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በስምምነቱ መሠረት የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት 657 መቀመጫዎች ይኖሩታል ማለት ነው፡፡

ሆኖም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር ከ550 መብለጥ የለበትም ስለሚል፣ የፓርቲዎቹን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ያስፈልጋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ የምርጫ ሕጎችና የምርጫ ሥርዓት ላይ እየተደራደሩ የሚገኙት ገዥው ፓርቲና አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመጀመርያው ዙር ድርድራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 578/2003 ለማሻሻል መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ባለፈው ዓርብ ባደረጉት ድርድር ደግሞ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ አዋጅ 532/99 ላይ ሲያደርጉ የነበረውን ውይይት፣ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡

በቀጣይ በምርጫ ቦርድ አወቃቀርና አደረጃጀት ላይ የጀመሩትን ድርድር ለመቀጠል፣ ለረቡዕ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.