30ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ

 (ኢዜአ)- 30ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የጉባኤው አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።

30ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ዓመታዊ ጉባኤ ከጥር 14 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የአስተባባሪው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለስ ደምሴ  እንደተናገሩት፤ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የተጣመረ ኮሚቴ ተዋቅሮ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ኮሚቴው የአገልግሎት አሰጣጥ፣የፀጥታና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከአራት ሺህ በላይ የህብረቱ አባል አገራት፣ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ታዛቢዎችና ሌሎች እንግዶች ተሳትፈውበታል።

በዘንድሮው ጉባኤ ላይም  በርካታ የአፍሪካ መሪዎች፣ከአፍሪካ ውጭ የሚገኙ አገራት ተጋባዥ ፕሬዝዳንቶች፣የተለያዩ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎችና የተለያዩ ልኡካን ቡድኖች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል።

እንግዶቹን ለማስተናገድ በመዲናዋ የሚገኙ  132 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ፣በርካታ ተሽከርካሪዎች ፣የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግጁ መደረጋቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።

ከፀጥታና ደህንነት አኳያም ኮሚቴው ቀደም ብሎ ዝግጅት እያደረገ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ነው የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መለስ የገለፁት።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በተለይም መሪዎች የሚንቀሳቀሱባቸው መንገዶች ስለሚዘጉ ህብረተሰቡ የተለመደ የእንግዳ ተቀባይነቱንና ትብብሩን እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።

29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፤ የወጣቶች ተጠቃሚነት፣ በአህጉሪቷ ሰላም ማስፈንና ሕብረቱን በፋይናንስ ማጠናከር የጉባኤው ዋነኛ የመወያያ አጀንዳዎች እንደነበሩ ይታወቃል።

የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ከአንድ አመት በፊት ከቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ  የተረከቡትን የሊቀመንበርነት መንበር በ30ኛው ጉባኤ ለሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሚ እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል።

በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት፣በሊቢያ የታየው የጥቁሮች የባርነት ንግድ ጉዳይ ፣ህብረቱን ከውጭ አገራት ተፅዕኖ ለማላቀቅ የተጀመረው የገቢ መሰብሰቢያ ስርዓት አፈጻጸምና የአፍሪካዊያን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውህደት ስራዎች በጉባኤው በስፋት የሚመከርባቸው አጀንዳዎች ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.